ለብሩህ ነገዋ በአዲስ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
ለብሩህ ነገዋ በአዲስ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ
ለብሩህ ነገዋ በአዲስ ምዕራፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ
በሙሴ መለሰ
ረጅም ታሪክ፣ቱባ ባህልና ሕብረ-ብሔራዊነት መለያዋ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ የነገ ተስፋዋን አስተማማኝ ለማድረግ አዲስ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል ይበልጥ ብሩህ ለማድረግ ሀገራዊ ምክክር ቁልፍና ታሪካዊ ሚና ይጫወታል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ስራ ያጠናቀቀ ሲሆን ነገ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በይፋ ይጀመራል።
ኮሚሽኑ በመላ ሀገሪቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሰበሰቡትን ሀሳቦችን በማደራጀት ለዋናው ሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን በይፋ ለይቷል።
እነዚህም የሀገር ግንባታ ታሪካዊ ሂደቶች፣ የመንግስት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ስርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም የሰላም ግንባታ ናቸው።
ስምንቱን መሠረታዊ አጀንዳዎች መነሻ በማድረግ የሚደረገው ውይይት፣ የፖለቲካ መረጋጋትን ከመፍጠር ባለፈ ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገትና ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ምክክሩ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው።ባለፉት የታሪክ ሂደቶች የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ ውይይት በመፍታት፣እርስ በርስ ለመደማመጥ እና ታሪካዊ ቁስሎችን በይቅርታ ለመፈወስ የሚያስችል ዋነኛ መንገድ ነው።
ከጠመንጃና ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሀሳብ የበላይነት የሚነግስበትን፣አለመግባባቶችና ልዩነቶች በሰላማዊ ውይይትና በንግግር የሚፈቱበትን ባህል ያሰፍናል።ይህም ልዩነቶችን በመቀበል በአንድነትና በጋራ መኖር የሚያስችሉ የጋራ እሴቶችና ሀገራዊ መግባባቶች ለማጠናከር ይረዳል።
ከዚህም ባለፈ፣ምክክሩ ለተቋማዊ እድገትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ለመድረስ መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነገ የሚጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ አስመልክቶ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምክክሩ ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው ሲሉ ገልጸውታል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፣ዛሬ ሀገራችን የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሀሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀትና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው ያሉ ሲሆን እኛ ዛሬም እንደ ትናንቱ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ማሸነፍ አይቀሬ ነው ብለዋል።
ይህንን በጎ ዕድል ለመጠቀምም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንነትና በኃላፊነት ስሜት በመሳተፍ ለሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያን መጻኢ ዕድል በራስ አቅምና ጥበብ ለመወሰን የሚያስችል ትልቅ እድል ነው።የኢትዮጵያ መጻኢ ተስፋና ሁለንተናዊ ብልጽግና ከሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ጋር የተሳሰረ ነው።
ባለፉት የታሪክ ሂደቶች ውስጥ የተፈጠሩ ቅሬታዎችን በንግግር መፍታት፣ከኃይል አማራጭ ይልቅ የሃሳብ የበላይነት የሚነግስበትን ምቹ መደላድል ይፈጥራል።
ዛሬ በምክክሩ ጠረጴዛ ዙሪያ የሚታየው የመነጋገር እና የመደማመጥ ባህል እንዲሁም ችግሮችን በውይይት ብቻ የመፍታት አማራጭ የተሻለች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ ታሪካዊ መሰረት ይጥላል።