በምስራቅ ቦረና ዞን የገቢ አሰባሰብን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን የገቢ አሰባሰብን ዲጂታላይዝድ በማድረግ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል
ነገሌ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን የገቢ አሰባሰብ ሒደቱን ዲጂታላይዝድ በማድረግ በበጀት ዓመቱ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የዕቅድ፣ በጀት ክትትልና ግምገማ ባለሙያ መዓዛ አሊ እንዳሉት በዞኑ የገቢ አሰባሰብ ሒደት ቀልጣፋና ፍትሐዊ ለማድረግ የዲጂታል አሠራር ተዘርግቷል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ ርዕሶች ለመሰብሰብ ከታቀደው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ከዞኑ የተሰበሰበው ዓመታዊ ገቢ ከዕቅዱ በ311 ሚሊዮን 917 ሺህ ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
የገቢ አሰባሰቡን ውጤታማ ለማድረግም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሠራር መዘርጋቱና ግብር መክፈል የዜግነት ግዴታ መሆኑን ተከታታይ የግንዛቤ መድረክ መፈጠሩን አንስተዋል።
ግብራቸውን በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ድርሻቸውን መወጣታቸውን ያስረዱት ደግሞ በነገሌ ቦረና ከተማ የሕንጻ መሣሪያ አቅራቢና አከፋፋይ አቶ ወርቁ ኦዳ ናቸው።
የሚከፍሉት የሥራ ግብር ለመሠረተ ልማት ግንባታ በመዋል ተመልሶ ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘባቸው ግብርን በጊዜ መክፈላቸውን አክለዋል።
በከተማው በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ቢኒያም አሰፋ በበኩላቸው ግብርን መክፈል የዜግነት ግዴታ እና ለአገር ልማት ነው ብለዋል፡፡
በታማኝነት ግብር መክፈል ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣም አስተያየታቸውን አጋርተዋል።
የሚከፍሉት ግብር ለአገር ልማት የራሱ ድርሻ እንዳለው የጠቆሙት ደግሞ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ሰይድ በድሩ ፤በታማኝነት ግብራቸውን በመክፈል ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍንና የሕዝቡ የመሠረተ ልማት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የበኩላቸውን መወጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡