የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራን ስኬታማነት ለማስቀጠል ግንዛቤን የመፍጠርና ህዝቡን የማነሳሳት ሚናቸውን ይበልጥ ሊያጎለብቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራን ስኬታማነት ለማስቀጠል ግንዛቤን የመፍጠርና ህዝቡን የማነሳሳት ሚናቸውን ይበልጥ ሊያጎለብቱ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች የአረንጓዴ አሻራን ስኬታማነት ለማስቀጠል ግንዛቤን የመፍጠርና ህዝቡን የማነሳሳት ሚናቸውን ይበልጥ ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር ገለጹ።
የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለና እስካሁን ባሉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ያስቻለ ነው።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሀሳብ የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረእግዚአብሔር፣ መገናኛ ብዙኃን የትውልድ ግንባታን በማከናወን፣ የጋራ መግባባት በመፍጠር እና የአንድነት እሴቶችን በማጠናከር በኩል ጉልህ አበርክቶ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ረገድ መገናኛ ብዙኃን የመረጃ ስርጭት ስራዎችን በማከናወን ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ በማነሳሳት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገበቻቸውን ተጨባጭ ስኬቶች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ ረገድ መገናኛ ብዙኃን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው ዓመት የተያዘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግብ ለማሳካት፣መገናኛ ብዙኃን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች እያከናወኑት ያለውን ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዲባባ በበኩላቸው፣ መገናኛ ብዙኃን ስለ መርሐ ግብሩ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙኃኑ መረጃን ለሕዝብ ከማድረስ በዘለለ፣ በተግባር በመሳተፍ ችግኞችን በመትከል የበኩላቸውን አሻራ እያሳረፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዘላለም እንዳሻው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የምግብ ዋስትናን አስተማማኝ ለማድረግ ያለው ፋይዳ እጅግ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም መርሐ ግብሩ የጋራ እሴቶቻችንን በማጠናከር አንድነታችንን የምናሳይበት እና ለጋራ ብሔራዊ ትርክት መገንቢያ የሚሆን ትልቅ አቅም ያለው መነሳሳት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቻናል ዋን ፕሮግራም አቅራቢ ሊያ ሳሙኤል፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለትውልድ የሚሸጋገር እና የሀገርን ልማት የሚያረጋግጥ አበይት ስራ መሆኑን ገልጻለች።
በዚሁ አጋጣሚ በመርሐ ግብሩ መሳተፍ ትልቅ ዕድል መሆኑንም ተናግራለች።
የፊልም ባለሙያው ቴዎድሮስ ተሾመ፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል፣ የአፈር መሸርሸርን ለመቆጣጠር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ ያለው ብሔራዊ ተነሳሽነት መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም በአረንጓዴ የተሸፈኑ ስፍራዎች ለመንፈስና ለአካል ደህንነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሆናቸውን በመግለጽ የዘርፉን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቷል።
አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋን ለመጨመርና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚከናወን ፋይዳ ያለው ስራ መሆኑን ገልጿል።
የኪነጥበብ ባለሙያዎችም በዘመቻው በንቃት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን በበኩሉ፣ ተፈጥሮን መንከባከብ ከፈጣሪ የተሰጠ ታላቅ ኃላፊነት መሆኑን አስረድቷል።