ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአብሮነትና የመረዳዳት እሴትን እያጎለበተ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር የሚሊዮን ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የአብሮነትና መረዳዳት እሴትን እያጎለበተ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ። 

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የክረምት በጎ ፈቃድ የነፃ ጤና ምርመራና የሕክምና አገልግሎት መርሃ ግብር አስጀምሯል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በማህበራዊ ዘርፍ የሚከናወኑ የጤና ምርመራዎች፣ የደም ልገሳ መርሐ ግብሮችና ሌሎች የሕክምና አገልግሎቶችም የዜጎችን ህይወት በመታደግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የልማት አጋዥ ኃይል እየሆነ መምጣቱንም አንስተዋል።

በተለይም የአቅመ-ደካሞችን፣ የአረጋዊያንንና የሀገር ባለውለታ ዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ የእርስ በርስ የመረዳዳት ባህልን እያጎለበተ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማስፋት የአብሮነትና የመረዳዳት እሴት የትውልድ ባህል እንዲሆን በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የዜጎችን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና ምርመራ፣ በደም ልገሳና ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የቅድመ መከላከል አገልግሎት ተደራሽነት በማስፋት የጤና ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያዘው የክረምት ወቅት የሚከናወነው የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ20 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም