የአርባ ምንጭ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአርባ ምንጭ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እየፈታ ነው
አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፡-የአርባ ምንጭ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግስታዊ አሰራርን በማቀናጀት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንደፈታላቸው ተገልጋዮች ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ክላስተር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች እንዳሉት የማዕከሉ ቀልጣፋ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል፡፡
ከተገልጋዮቹ መካከል ፓስፖርት ለማውጣት በማዕከሉ የተገኙት አቶ ገብረእግዚአብሔር ሃይለስላሴ በማዕከሉ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸው ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ አስችሏቸዋል።
ይህም ቀደም ሲል በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ሲስተዋል በነበረ መጓተት ይፈጠር የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር መፍታት ችሏል ብለዋል።
የማዕከሉ ሠራተኞች አክብሮት የተሞላበት አገልግሎት እንደሰጧቸው ገልጸው፣ በማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶች መስጠታቸው ጊዜ፣ ወጪና እንግልትን አስቀርቶልናል ብለዋል።
አገልግሎቱ በዲጂታል ሥርአት የታገዘ መሆኑ ቀልጣፋና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት በፍትሀዊነት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።
ዜጎችን ለምሬት ይዳርግ የነበረውን የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ያስተካከለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ዘላለም አሸናፊ ናቸው።
የአገልግሎቱ ቀልጣፋና ውጤታማነት መንግስት አሰራሩን በማዘመን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳየበት ነው ብለዋል።
እሳቸውም የንግድ ፈቃዳቸውን ለማውጣት በመጡበት ወቅት ወደ ተለያዩ ተቋማት መሄድ ሳያስፈልጋቸው አገልግሎቶቹን ከመሶብ አገልግሎት ብቻ በተሟላ ሁኔታ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ክላስተር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ይበቃል አሰፋ በበኩላቸው በማዕከሉ አምስት የክልልና አራት የፈደራል ተቋማት 32 አይነት አገልግሎቶች በዲጅታል ታግዘው እየተሰጡ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም ዜጎች ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ከእንግልት፣ ከእጅ መንሻና መሰል ችግሮች እንደታደጋቸው ገልጸዋል።
አሰራሩ መዘመኑ ስራን ከማቀላጠፍ ባለፈ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በዘላቄታው ለመፍታት አስችሏል ብለዋል።