ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትን በማስፋት አምራች ዜጋ ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስመዝግበዋል

ጂንካ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት አምራች ዜጋ ለመፍጠር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስመዝገባቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በ2018 በጀት ዓመት የጤና አገልግሎት ዕቅድ አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።


 

መድረኩ እየተካሄደ ያለው “ከቤተሰብ እስከ ጤና ተቋም፤ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የግምገማ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ እንደገለጹት፤ በክልሉ ፍትሐዊና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።

ለዚህም የጤና ተቋማትን የሰው ኃይል ማብቃትና ዘመናዊ የሕክምና ግብአቶችን ማሟላት ላይ በቅንጅት መሠራቱን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እና ሥርዓተ-ምግብ፣ በበሽታ መከላከልና ጤናን ማጎልበት እንዲሁም ዘርፈ-ብዙ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ላይ በትኩረት መሠራቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በእናቶችና ሕፃናት ሞት ቅነሳ የተደረጉ ጥረቶችም በሰለጠነ ባለሙያ የመውለድ ምጣኔን ወደ 86 በመቶ ማሳደጋቸውን  ገልጸዋል።

በመድረኩ የክልሉ የጤና ተቋማት ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም