ቀጥታ፡

በክልሉ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 6/2018(ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም  በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት እየተገኝባቸው መሆኑ ተገለጸ።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ በ2018 በጀት ዓመት በማኅበራዊ ክላስተር የተከናወኑ የሥራ አፈጻጸሞችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በክልሉ የማኅበራዊ ክላስተር ዘመናዊነትንና ተወዳዳሪነትን የሥራው መመሪያ አድርጎ  ባከናወናቸው ተግባራት ታላላቅ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

ተወዳዳሪና በራሱ የሚተማመን ትውልድ ለማፍራት በተከናወናወኑት ተግባራት  ከታችኛው እርከን ጀምሮ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ12 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ገበታቸው ላይ እንደነበሩ አስታውሰው በዚሁ ወቅት ከ2 ሺህ 900 በላይ 'ቡኡራ ቦሩ' የተሰኙ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ በተለይም መንግሥትና ማኅበረሰቡ በማቀናጀት በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።

የተማረና ድህነትን የሚያሸንፍ ትውልድ ለማፍራት  የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

በትምህርት ዘመኑ ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ መጻሕፍትን ማቅረብ የተቻለ ሲሆን ትምህርትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍም የዲጂታል ፓርኮችን በማስፋፋት ረገድ አበረታች ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ የመምህራን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ተችሏል ያሉት አስተባባሪው በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ሲታይ የነበረውን ችግር ለመፍታት መልካም እንቅስቃሴ መኖሩን አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በጤና ዘርፍ የተከናወኑ ሥራዎችም የተሻለ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን አመልክተው በተያዘው ዓመትም በርካታ ሰዎች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አባል መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል።

የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የማኅበረሰብ ፋርማሲዎችን ለማስፋፋት በተከናወኑ ተግባራትም  750 የማኅበረሰብ ፋርማሲዎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

በዚሁ ወቅት  በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥም ጥረት ተደርጓል ነው ያሉት።

ወጣቶች የልማትና የሰላም ኃይል እንዲሆኑ በተከናወኑ ተግባራትም እንዲሁ የኢኮኖሚ ጥገኝነትን አስወግደው በልማትና በሰላም ግንባታ ሥራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት እንዲሳተፉ ተደርጓል ሲሉም ገልጸዋል።

የቀድሞ ባህላዊ እሴቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ በተከናወነው ሥራም የባህል ዘርፉን የማስተዋወቅ እና የማልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም