ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በሳይንሳዊ መረጃ የተደገፈ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመከላከል አቅም ገንብቷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና ቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከርና የጤና ስርዓቱን በሳይንሳዊ መረጃ በመደገፍ  የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከል የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት 100ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ከመጪው ሐሙስ ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚያከብር አስታውቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ ከምስረታው ጀምሮ ለአንድ ምዕተ ዓመት የተለያዩ የህብረተሰብ ጤና አገልግሎቶችን ሲሰጥ ቆይቷል። 

አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለመብቃትም ባለፉት መቶ ዓመታት በተለያዩ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች ውስጥ ማለፉን ገልጸዋል።

በቆይታውም የተለያዩ ክትባቶችን በማምረት፣ ሳይንሳዊ ምርምሮችን በማካሄድ፣ እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን ቀድሞ በመለየት ፈጣን ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል። 

በተጨማሪም ኢንስቲትዩቱን በሕግ፣ በአሠራርና በሰው ኃይል በማጠናከር የሕብረተሰብ ጤና ቁጥጥር ስርዓቱን የማዘመንና ተደራሽነቱን የማስፋት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የቅኝት ስርዓቱን የማጠናከርና የጤና ስጋቶችን በመተንተን ስልታዊ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የድንበር ተሻጋሪ በሽታዎች ቁጥጥር ስርዓቱንም ዓለም አቀፍ የጤና ደንቦችን በተከተለ አግባብ በመምራት ቀልጣፋና የተናበበ ቁጥጥር ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል። 

በዚህም ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ7 ሚሊየን በላይ መንገደኞች ላይ በኢንስቲትዩቱ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ባለሙያዎች ክትትል መደረጉን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ሥርዓቱንና የጤና ደህንነትን የማጠናከር ስራ በስፋት መሰራቱንም ጨምረው ገልጸዋል። 

በጤና ስጋቶች ላይ ምርምርና ቅኝት በማድረግ፣ ብሎም ሳይንሳዊ መረጃዎችን በማመንጨት ለስልታዊ እቅዶችና ተግባራት እንዲውሉ በማድረግ የጤናው ዘርፍ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ያለውን ሚና ለማጎልበት መስራቱንም አብራርተዋል። 

የላቦራቶሪ አገልግሎት አቅምንና ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውንም አስረድተዋል።

በቅኝት ስርዓት በሽታዎችን በመለየት፣ በላቦራቶሪ የዘረመል ትንተና በማድረግና የፈጣን ምላሽ ስርዓቱን በማጠናከር የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር የሚችል አቅም መገንባቱን ዶክተር መሳይ ገልጸዋል። 

ለአብነትም በቅርብ ዓመታት የተከሰቱትን የዝንጀሮ ፈንጣጣ (Mpox) እና የማርበርግ ቫይረስን በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ሳይዛመቱ በአፋጣኝ መቆጣጠር መቻሉን በምሳሌነት አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም