ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሁለት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ):-ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሁለት የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ።

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዷል።


 

ምክር ቤቱ በዛሬው ስብሰባው በኢትዮጵያ እና በጣሊያን ሪፐብሊክ መንግሥት፣ እንዲሁም ከዓለም ባንክ ለሦስተኛው የኢትዮጵያ ዕድገትና ልማት ፖሊሲ ክንውን ጋር በተጣጣመ መልኩ ለዘላቂ እና አስተማማኝ ልማት ለኢትዮጵያ የሚሰጥ የበጀት ድጋፍ ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) የብድር ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ የብድር ስምምነቱ 70 ሚሊዮን ዩሮ ሲሆን ምንም ዓይነት የአገልግሎት ክፍያ እንደማይጠየቅበት ገልጸዋል።

ብድሩ ቀጥታ ወደ መንግሥት በጀት ፈሰስ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመው፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራውን በማሳለጥ ዕድገትን ለማፋጠን አጋዥ ነው ብለዋል።

የብድር ስምምነቱ 16 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለው ሲሆን፣ በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ የረጅም ጊዜ ብድር መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የብድር ስምምነቱን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።


 

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በፈረንሳይ መንግሥት መካከል የትዕዛዝ ቁጥጥርና ንብረት አስተዳደር ሥርዓቶችን የደረጃ አወጣጥ የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነትን መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ስምምነቱ 54 ሚሊዮን 600 ሺህ ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነትን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

የብድር ስምምነቱ በ10 ዓመት የችሮታ ጊዜ ውስጥ በ25 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቅሰው የወለድ መጠኑም 0 ነጥብ 347 በመቶ ዝቅተኛ መጠን ያለው መሆኑን አብራርተዋል።

የብድር ስምምነቱ የኢትዮጵያን ዲጂታላይዜሽን ጉዞ የሚያፋጥን እንደሆነም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም