ቀጥታ፡

በክልሉ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በ2018 የበልግ አዝመራ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡም ተገልጿል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በዚሁ መሰረት ባለፉት ዓመታት አርሶና አርብቶ አደሩ በሁሉም የአርሻ ወቅቶች በግብርና ልማት ሥራ ላይ እንዲሰማራ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በተያዘው የምርት ዘመን በበልግ ወቅት በተለይም በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደሮች በግብርና ሥራ ላይ በስፋት በመሳተፍ፣ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ገበያውን ለማረጋጋት የሚያግዙ ተግባራትን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ በ2018 በልግ አብቃይ በሆኑ ዞኖች ወደ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን አመልክተዋል።

ለአርሶ አደሩ ድርቅን መቋቋም የሚችሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የስንዴ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ እና ዳጉሳ ያሉ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎች እንዲቀርቡ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በክልሉ የበልግ እርሻ በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ሐረርጌ፣ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ እና ቦረና ዞኖች በዋናነት ተጠቃሽ እንደሆኑም አቶ በሪሶ አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በበልግ የለማው ሰብል ደርሶ መሰብሰብ መጀመሩን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ እስካሁን በ500 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማው ሰብል መሰብሰቡን አረጋግጠዋል።

ለበልግ አዝመራው ስኬታማነት የክልሉ ግብርና ቢሮ የአፈር ማዳበሪያና የተለያዩ የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችን በወቅቱ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማቅረቡን ገልጸው፤ ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ሰብል አሰባሰብ ድረስም ያልተቋረጠ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።

ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የክልሉ መንግስት የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የተተገበሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና የተደረጉ ሁለንተናዊ ድጋፎች በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘታቸው ተመልክቷል።

ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የወተት ላሞች እርባታ በዘመናዊ መንገድ መተግበሩና ምርጥ የእርባታ ዶሮዎች ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸው መሆኑ ተመላክቷል።

በዓሣ እርባታም የዓሣ ጫጩቶች ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተሰራጭተው ወደ እርባታ ኩሬዎች መግባታቸውን ነው የተገለጸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም