ቀጥታ፡

በሰለጠነ ንግግር፣በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

‎አዲስ አበባ፤ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሰለጠነ ንግግር፣በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ለታሪካዊውና ታላቁ የሀገራዊ ምክክር በምትሰናዳበት በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት፤ለመላው የሀገሬ ልጆች የማስተላልፈው ታላቅና የከበረ ጥሪ አለኝ ብለዋል።

ይህም በነገው እለት የሚጀመረው ውይይት ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ የእኛን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው ያሉት።

‎ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣መረጋጋትና ሁለንተናዊ ብልጽግና የምትተጉ፣ የኢትዮጵያ ታላቅነት ግድ የሚላችሁ ሁሉ፤ ፈረሱም ሜዳውም ይኸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

‎ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ለሀገር ነጻነት፣ለሉዓላዊነትና ለክብር ሲሉ በደማቸውና በአጥንታቸው እንደተዋደቁላት ሁሉ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚሸከሙ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትፈልጋለች ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፥ሆኖም ዛሬ ሀገራችን የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሀሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀትና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው ያሉ ሲሆን እኛ ዛሬም እንደ ትናንቱ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ እንገኛለን፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ማሸነፍ አይቀሬ ነው! ሲሉ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በሰለጠነ ንግግር፣በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም