ማን የፍጻሜውን ትኬት ይቆርጣል? ፈረንሳይ ወይስ ስፔን? - ኢዜአ አማርኛ
ማን የፍጻሜውን ትኬት ይቆርጣል? ፈረንሳይ ወይስ ስፔን?
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከሁለት ቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ በግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር ይመለሳል።
ፈረንሳይ እና ስፔን ምሽት አራት ሰዓት ላይ በዳላስ ስታዲየም ለፍጻሜ ለማለፍ የሚያደርጉት ፍልሚያ የዓለም ትኩረት አርፎበታል።
ፈረንሳይ በሩብ ፍጻሜው ሞሮኮን 2 ለ 0 በመርታት ለሶስት ተከታታይ ዓለም ዋንጫ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።
የሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ፈረንሳይ ግማሽ ፍጻሜ ስትገባ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚዋ ስፔን ቤልጂየምን 2 ለ 1 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለች ሲሆን አራት ውስጥ ስትገባ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ከዚህ ቀደም አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።
ጀርመን እ.አ.አ በ2006 ባዘጋጀችው 18ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ 16 ውስጥ ተገናኝተው ፈረንሳይ ስፔንን 3 ለ 1 በመርታት ለሩብ ፍጻሜው አልፋለች።
ፍራንክ ሪቤሪ፣ ፓትሪክ ቪዬራ እና ቲዬሪ ሄነሪ በወቅቱ ለፈረንሳይ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ነበሩ።
ዴቪድ ቪያ የስፔንን ብቸኛ ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል።
የአውሮፓ የእግር ኳስ ኃያላኑ ከ20 ዓመታት በኋላ በዓለም ግዙፉ የእግር ኳስ መድረክ ለፍጻሜ ለማለፍ ይፋለማሉ።
በአጠቃላይ ሁለቱ ሀገራት በሁሉም የውድድር እና የወዳጅነት ጨዋታዎች 38 ጊዜ ተገናኝተው ስፔን 18 ጊዜ ስታሸንፍ ፈረንሳይ በ13ቱ ድል ቀንቷታል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ስፔን በ38ቱ ጨዋታዎች ላይ 71 ግቦችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ፈረንሳይ 45 ጎሎችን ማስቆጠር ችላለች።
ሁለቱ ሀገራት በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በአማካይ ከሶስት ጎሎች በላይ የሚቆጠር ሲሆን ይህም ቡድኖቹ ለማጥቃት እንቅስቃሴ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ ነው።
በዓለም ዋንጫው ላይ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው የ27 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ በዛሬ ጨዋታ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው።
ምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር ከአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ጋር በጎል እኩል በመሆን ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ብልጫ ወስዶ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።
በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ 20 ጎሎች ከመረብ ላይ በማሳረፍ በምንጊዜም ከፍተኛ አስቆጣሪነቱ ከሜሲ (21 ጎል) በአንድ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ምባፔ በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ 12 ጎሎችን በማስቆጠር በውድድሩ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አምስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፈው ኡስማን ዴምቤሌ እና አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ያቀበለው ማይክል ኦሊሴም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾች ናቸው።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አራት ጎሎችን ያስቆጠረው የ29 ዓመቱ አጥቂ ሚኬል ኦያርዛባል ከስፔን በኩል ትኩረትን የሳበ ተጫዋች ሆኗል።
በዓለም ዋንጫው አንድ ግብ ያለው ላሚን ያማል እና የቡድኑ አምበል ሮድሪ የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
ፈረንሳይ ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ለአምስተኛ፣ ስፔን ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለማለፍ ይጫወታሉ።
ጨዋታው ተመጣጣኝ እና አዝናኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ ከአርጀንቲና እና እንግሊዝ አሸናፊ ጋር በፍጻሜው ይገናኛል።