በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ2019 በጀት አመትያጸደቀው በጀት በከተማዋ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤው የከተማ አስተዳደሩን ለ2019 በጀት ዓመት 502 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር በጀት አፅድቋል።
የከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ለ2019 በጀት ዓመት 502 ነጥብ 27 ቢሊዮን መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ድልድሉ የመደበኛ በጀትን በቁጠባ ጥቅም ላይ እንዲውል ታሳቢ በማድረግ የበጀት ጭማሪው በዋናነት ለካፒታል ፕሮጀክቶች እንዲሆን መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት የካፒታል በጀቱን 71 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን መደበኛ ወጭ ከአጠቃላይ በጀቱ 25 ነጥብ 3 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
በጀቱ በዋናነት እድገት ተኮር በሆኑ ዘርፎች እንዲውል በማድረግ ሰፋፊ የሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ ለማጠናከር ነው ብለዋል።
በዓይነት እንዲሁም በመጠን ሰፋፊ የከተማ ግንባታና የመልሶ ማልማት ስራዎችን በማከናወን የከተማዋን እድገት ለማሳለጥ ነው ብለዋል።
በጀቱ የከተማዋን የልማት ፍላጎትና የአገልግሎት ደረጃ ይበልጥ ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተመደበ ሲሆን፣ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል እንደሆነ አመላክተዋል።
በተጨማሪም ለማህበራዊ ልማት፣ ለውሃ አቅርቦትና ሁሉንም አቀፍ የልማት ሥራዎች በተሳለጠ መንገድ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከፍተኛ ድርሻ የያዘው የካፒታል በጀቱ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለቤት ልማት፣ ለመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የትራንስፖርት አገልግሎትን ማሻሻልና አጠቃላይ የከተማዋን ልማትና ዕድገት ይበልጥ ለማዘመን የተመደበ እንደሆነ ገልፀዋል።