ቀጥታ፡

ፌዴራል ፖሊስ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የወንጀል መከላከልና ቁጥጥር ሥርዓትን በመተግበር፣ የሀገርን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እያስጠበቀ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 6/ 2018 (ኢዜአ)፦ፖሊስ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ የወንጀል መከላከልና ቁጥጥር ሥርዓትን በመተግበር የሀገርን ሰላምና ደህንነት የማጽናት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወንጀልን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ በርካታ ስኬታማ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል። 

ከለውጡ ወዲህ የተከናወነው ተቋማዊ ሪፎርም የሀገሪቱን ጸጥታ በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲገነባ በማድረግ የፖሊስን ተልዕኮ የመፈጸም አቅም በእጅጉ እንዲያድግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል። 

በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና የአደባባይ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቃቸው የተቋሙ የተቀናጀ የጸጥታ ስራ ውጤታማነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የውስጥ እና የውጭ እኩይ ተልዕኮዎችን በቅድመ መከላከል ጥረት በማምከን፣ የህግ የበላይነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ 

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ሂደት እና በድህረ ምርጫ ወቅት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ተቋሙ የላቀ ሚና መጫወቱንም አስረድተዋል፡፡ 


 

የሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ስራዎች የሀገሪቱን የልማት ጉዞ በስኬት ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር ድንበር ዘለል ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ፣ ኮንትሮባንድ እና የገንዘብ ዝውውሮችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም የጸጥታ ስራውን በጋራ በማቀናጀት የሀገርን ደህንነት በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል፡፡ 

ተቋማዊ ሪፎርሙ የፖሊስን የአሰራር ሂደት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማዘመንና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ በማድረግ የተቋሙን ብቃት ከፍ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡ 

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተዘረጉት ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎች ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ጋር መተሳሰራቸው ወንጀልን ቀድሞ የመከላከል አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን ጠቅሰዋል፡፡ 

የፎረንሲክ ላብራቶሪውን በዘመናዊ መሣሪያዎችና በሰለጠነ የሰው ኃይል ማጠናከር የሳይበር ወንጀል፣ የሐሰተኛ ሰነድ እና የዲጂታል ማጭበርበር ምርመራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማከናወን መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡ 

ፖሊስ በበጀት ዓመቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የወንጀል መከላከልና መቆጣጠር ስርዓትን በመተግበር ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚቃጡ እኩይ ተልዕኮዎችን በቅድመ መከላከል በማምከን ሀገርን የማጽናት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት በማጠናከር፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስጠበቅና የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥ ኢትዮጵያን የማጽናት ጉዞውን አጠናክሮ እንሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡ 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም