የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ መጥቷል
ድሬደዋ፣ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፡- የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን የመደጋገፍ ባህል እያጎለበተ መምጣቱ ተገለጸ።
በድሬዳዋ አስተዳደር "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የክረምት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ዋና ተጠሪ ኢብራሂም ዩሱፍ በወቅቱ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የከተማዋን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት አግዘዋል።
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ ከዋኝ ወጣቶችም ድሬዳዋ ተገኝተው በአረንጓዴ አሻራና በአረጋውያን ማዕከላት በጽዳትና እንክብካቤ ያከናወኑት በጎ ስራ የሚመሰገን መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በጎ ፈቃደኞቹ በቤቶች ግንባታ፣ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና በሌሎች ተግባራት በንቃት በመሳተፍ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ የመደጋገፍ ባህል እንዲዳብር አድርገዋል ብለዋል።
ዘንድሮ በከተማዋ በሚካሄደው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚያወጡ የልማት ስራዎች በማከናወን 300 ሺህ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ የገጠርና የከተማ ወጣቶች ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል ።
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ከ400 በላይ የአረጋዊያን ቤቶች ግንባታ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ ወጣት እንደገና ፈቃዱ እንደገለፀው፤ በድሬደዋ አስተዳደር ገጠርና ከተማ የችግኝ ጉድጓድ ቆፋሮና ችግኝ በመንከባከብ ፣ ደም በመለገስና አረጋዊያንን መኖሪያ በማፅዳት የተሳካ ስራ መስራታቸውን አስታውቋል።
ወጣት ሁሴን አህመድ በበኩሉ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሻገር ወጣቶች በየሚጓዙበት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻቸውን ለመወጣት እያስቻለ መሆኑን ገልጿል ።
በድሬደዋ ቆይታችን በከተማዋ ከሚገኙ ወጣቶች እና አመራሮች ጋር ያከናወናቸው ተግባራትና ውይይት በቀጣይ የተሻለ ግንኙነትና ትስስር በመፍጠር ቀጣይነት ያለው ስራ ለመስራት እንዳስቻላቸው የገለፀችው ደግሞ ወጣት ሜሮን ሽመልስ ናት።