የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው
አዳማ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፡-የጤና መድህን አገልግሎትን ለሁሉም ማህበረሰብ ምቹ በማድረግ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ የአንድ ቋት ክፍያ አተገባበርና ገቢን መሰረት ያደረገ የጤና መድህን መዋጮ ውጤታማነት ላይ ያተኮረ የክልል ጤና ቢሮዎች አመራሮች፤ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ወርቁ፤ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱን የተሳለጠና ቀልጣፋ ለማድረግ የአንድ ቋት የፋይናንስ ክፍያ ስርዓት ተግባራዊ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም መሆኑ በወረዳ ደረጃ የነበረውን የተበታተነ የፋይናንስ ቋት ወደ ዞን በማሳደግ የተሻለ የፋይናንስ አቅም እንዲፈጠር አስችሏል ብለዋል።
በዞን ደረጃ ከፍ ያለ የፋይናንስ ቋት በመመስረቱ ውል የተገባላቸው የህክምና ተቋማት ለኢንሹራንስ አባላቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እያስቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ይህም የገቢ አቅምን መሰረት ያደረገ የጤና መድህን መዋጮ መመሪያ በማዘጋጀት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ አባላት የተናጥል ድጎማ በማድረግ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ለፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የጤና መድህን ተደራሽነቱ 96 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው በአዲሱ በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት እንዷለም፤ የአንድ ቋት ክፍያ ላይ ውጤታማነትና ገቢን መሰረት ያደረገ የጤና መድህን መዋጮ ስርዓት ላይ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት አሁን ላይ በ67 ዞኖች የአንድ ቋት የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ለጤና ተቋማት ዞኖች ለመክፈል ያጋጥማቸው የነበረውን የፋይናንስ እጥረት ማቃለል ተችሏል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሙንጣሻ ብርሃኑ፤ በክልሉ የጤና መድህን ሽፋን 85 በመቶ መድረሱን ገልጸው ገቢን መሰረት ያደረገ የክፍያ ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በክልሉ ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ተግባራዊ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ምትኩ ታመነ በበኩላቸው፤ አንድ ቋት የክፍያ አሰራር በመዘርጋት ወደ አገልግሎት በመገባቱ በየተቋማቱ አባላቱ ያጋጥማቸው የነበረውን የአገልግሎት ችግር መፍታት ተችሏል ብለዋል።
የጤና መድህን የአንድ ቋት የክፍያ ስርዓት ማለት ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች የገንዘብ መዋጮ በአንድ ማዕከላዊ ቋት ሆኖ የፋይናንስ እጥረትን በማቃለል የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር ነው።