ለአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ - ኢዜአ አማርኛ
ለአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር የሚደረገው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ
ጅግጅጋ፣ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በሰላም ግንባታ ላይ ይበልጥ በመትጋት ለአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገለጹ።
"ሰብዓዊ መብትና የሰላም ግንባታ" በሚል መሪ ሐሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ የጸጥታና ፍትሕ አካላት ጉባኤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፣ የክልል ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች፣ የማረሚያ ሃላፊዎችና እና የሕዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ተጨባጭ ለውጥ የመጣበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የተጠርጣሪዎችና የታራሚዎች አያያዝ በብዙ መልኩ ለውጥና መሻሻል የታየበት ስለመሆኑ ተናግረዋል።
እንደ አጠቃላይ በሰላም ግንባታ ላይ ይበልጥ በመትጋት ለአጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር መስጠፌ ሙሃመድ፤ በክልሉ ለሰላምና ጸጥታ እንዲሁም ለሰብአዊ መከበር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፣ ለማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቀውስ የጸጥታ መደፍረስ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ በክልሉ አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ የመገንባት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።