ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)  ገለጹ።  

የግብርና ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረት የአህጉር-አቀፍ የእንስሳት ሃብት ቢሮ በመተባበር የተዘጋጀው ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 


 

የግብርና ሚንስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ፤ ኢትዮጵያ የእንሰሳት ሃብት ልማት በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ እየሰራች ነው።

በዚህም አርሶና አርብቶ አደሮች የሚያጋጥሟቸውን የውሃና የመኖ እጥረትን በዘላቂነት የሚቀርፉ እንዲሁም የእንስሳት ሕክምና መስጫ ተቋማትን የማስፋፋት ስራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ከአርብቶ አደሮች ጋር የሚሰሩ ተቋማትን፣ የእንስሳት ገበያ ማዕከላትን ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሸነት የማጠናከር ስራዎችንም እየተሰራበት እንደሆነም አብራርተዋል።

የአፍሪካ አርብቶ አደሮች ገበያ ልማት ላይ ያተኮረው ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት የግብርና-ምግብ ስርዓቶቻቸውን ለማጠናከር፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስር ያለውን የአህጉር ውስጥ ንግድ ለማስፋፋት እና የእንስሳት እና አርብቶ አደር የምርት ስርዓቶችን ሙሉ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመጠቀም በሚጥሩበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ የተዘጋጀ ነው ብለዋል። 

በአፍሪካ አገራት መካከል የእውቀት ሽግግሮችን ማጠናከር፣ ኢንቨስትመንቶችን ማስተባበር እና በመላው አፍሪካ የሚገኙ ማህበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ድንበር ተሻጋሪ መፍትሄዎችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የእንስሳት ሀብት ልማቱን ከማዘመን ፣ምርታማነትንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውንም ገልጸዋል።  


 

በአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ቢሮ ዳይሬክተር ሁያም ሳሊህ ( ዶ/ር)  አፍሪካ የዓለምን የእንስሳት ሃብት ከፍተኛ ድርሻ ብትይዝም፣ ከእሴቱ ግን የምታገኘው በጣም አነስተኛውን ድርሻ ነው ብለዋል።

በቀጣይም የአህጉሪቷን ግዙፍ የእንስሳት ሃብት በማልማት የአርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል በሁሉም ዘርፍ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ቢሮ የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከአጋር አካላት ጋር እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንም አንስተዋል። 


 

በአፍሪካ ህብረት የገጠር ልማት ክፍል ኃላፊ እና የግብርናና ምግብ ዋስትና ክፍል ተጠባባቂ ኃላፊ ጃኔት ኤደሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ የእንስሳት ልማት ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪ ማድረግ፣ ቀጣናዊ ውህደት እንዲሁም የግል ዘርፉ ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአፍሪካ የእንስሳት ገበያ ማዕከልና ሌሎች የእንስሳት ልማት ዘርፍ ኢንቨስተመንቶችን ማሳደግና ቅድሚያ በመስጠት  በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ነው የገለጹት። 

ከእንስሳት ውጤቶች ምርት ጀምሮ እስከ አገር ውስጥና የውጭ ገበያ ባለው ሂደት የእሴት ሰንሰለትን ማጠናከር የእንስሳት ጤና ጥበቃ ሥርዓትና  ድንበር ተሻጋሪ  የእንስሳት በሽታዎች ቁጥጥርም ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።


 

የጌትስ ፋውንዴሽን ተወካይ ቶማስ አቤ፤ ፋውንዴሽኑ የአርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት፣ የገበያ ተደራሽነት ለማስፋፋት፣ የፖሊሲ እና ተቋማዊ አቅሞችን ለማጠናከር ከአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ክፍል ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

የአፍሪካ አርብቶ አደሮችን  ገበያ ልማትና  ኢንቨስትመንት ለማሳደግና  የፖሊሲ ማዕቀፎችን ለማጠናከር እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችንም ጠቅሰዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም