ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጀርመን ዘላቂ የኢኮኖሚ እና ቀጣናዊ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ጀርመን ዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስራቸውን እና ቀጣናዊ አጋርነታቸውን ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጌዛ አንድሪያስ ፎን ጋየር (ዶ/ር) ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከሚኒስትር ዴኤታው ጋር በነበራቸው ውይይት ጀርመን የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት ትብብር እና የንግድ አጋር መሆኗን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በዓለም አቀፍ አጀንዳዎች ዙሪያም ያላቸው ተባብሮ የመሥራት ልምድ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ጌዛ አንድሪያስ ፎን ጋየር በበኩላቸው፤ ጀርመን የኢትዮጵያ ምርቶች ዋና መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፥ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በሰለጠነ የሰው ኃይል ሥምሪት፣በአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም እንዲሁም በወቅታዊ ቀጣናዊና መካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ዙሪያም ሀሳብ መለዋወጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም