ቀጥታ፡

በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሳውላ ፤ ሐምሌ 6/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

በክልሉ የወባ በሽታ እና በስርዓተ ምግብ አለመመጣጠን ችግር ምክንያት የሚከሰት በሽታን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በሳውላ ከተማ ተካሂዷል።


 

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በክልሉ የወባ በሽታን የመቆጣጠርና አክሞ ማዳን እንዲሁም ህፃናት በምግብ እጥረት ለሚከሰት በሽታ እንዳይጋለጡ  በመስራት አምራች ዜጋን ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

በተለይም የወባ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ውጤት እየታየ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ህዝቡን በባለቤትነት በማሳተፍ  የተጀመሩ ስራዎች  ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

ተግባሩን ከክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ጋር በማቀናጀት  ወጣቶች  በግንዛቤ ፈጠራና በአካባቢ ጥበቃ  ላይ እንደሚሰማሩም  ተናግረዋል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፣ የወባ በሽታን  ለመከላከል በአጎበር ስርጭት፣ ኬሚካል ርጭትና በአካባቢ ጽዳት ላይ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም የጤና ባለሙያዎች  በመረጃ አሰባሰብ፣ በቤት ለቤት ክትትል፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠርና በቅድመ መከላከል ሥራዎች ላይ አተኩረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ የክልል ፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር የመንግስት ስራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም