ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በበጀት ዓመቱ ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

ሰመራ፣ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ8 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

የአፋር ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ አወል አብዱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የክልሉን የገቢ ግብር አሰባሰብ ውጤታማ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ተሰርቷል።

ቅንጅታዊ ሥራውን ከማጠናከር ባለፈ አሰራርን የማዘመን ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፣ በእዚህም ውጤታማ የግብር አሰባሰብ ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል። 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ 8 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደሥራመገባቱን አስታውሰው፣ በበጀት ዓመቱ ከ8 ቢሊዮን 524 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መተግበሩ፣ የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ግንዛቤ እያደገ መምጣት እና በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ቁርጠኝነት ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።

ገቢው የተገኘው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆኑ ታክሶች እና ታክስ ካልሆኑ የገቢ አርዕስቶች መሆኑንም አስረድተዋል። 

እንደ አቶ አወል ገለጻ፣ ዘንድሮ የተገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት ከተገኘው ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው። 

በገቢ አሰባሰብ ላይ ቅንጅታዊ አሰራርን ከመተግበር ባለፈ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የተሰራው ሥራ ለውጤቱ አስተዋጾ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም