የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ድል የጋራ ጥረት፣ ትጋትና አንድነት ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ድል የጋራ ጥረት፣ ትጋትና አንድነት ውጤት ነው
ሀዋሳ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፡-የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ያስመዘገበው ድል የጋራ ጥረት፣ ትጋት እና አንድነት ውጤት መሆኑ ተገለጸ፡፡
የ2018 ዓ.ም ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግና ከ20 ዓመት በታች አሸናፊ የሆነው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዛሬ ሀዋሳ ከተማ ሲደርስ በከተማው ነዋሪዎችና በተለያዩ አካላት ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።
በአቀባበል ሥነስርአቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና የክልሉ ስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ በየነ በራሳ እንደተናገሩት ክለቡ ያስመዘገበው ስኬት የጋራ ትብብርና የአንድነት ውጤት ነው።
ክለቡ የህዝብ መሰረት ያለውና የሚደረግለትን ጠንካራ ድጋፍና ክትትል በአግባቡ በመጠቀም ስኬታማ መሆን እንደቻለ ያነሱት አቶ በየነ፣ አንድነትና ትጋት ካለ ለውጤት መብቃት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ክለቡ የተቀናጀ ድጋፍ በማግኘቱ ያስመዘገበውን ስኬት በአርአያነት ወስዶ በሌሎች የልማት መስኮችም ለመድገም መትጋት እንደሚገባ ገልጸው፣ ክለቡ ያስመዘገበው ውጤት ለክልሉ ህዝብም ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ክለቡ ሲበረታም ሆነ ሲደክም ከጎኑ በመሆን ላበረታቱት ደጋፊዎች ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ዓመት ክለቡ በአፍሪካ ሻምፕዮንስ ሊግ በሚኖረው ውድድር የላቀ ውጤት እንዲያስመዘግብ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊና የክለቡ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው፣ ክለቡ ያስመዘገበው ድል የህዝቡ አንድነት፣ ትጋትና ጥረት ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
የተጨዋቾች ትጋት፣ የክልሉ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም የደጋፊዎች አስተዋጾ ክለቡን የድል ባለቤት እንዳደረገው ገልጸው፣ ባለድርሻ አካላት ላደረጉት የተቀናጀና ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ክለቡ ያስመዘገበው ድል በክልሉ በስፖርት ልማት ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያሳድግና መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው ተተኪ ስፖርተኞች በበቂ ሁኔታ ለማፍራት ይሰራል ብለዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ማልማትና ስፖርቱ ከመንግስት ድጋፍ ተላቆ የራሱ ሀብትና የገንዘብ ምንጭ እንዲኖረው የሁሉም ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።