ቀጥታ፡

ዲጂታል የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባ ትክክለኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ወሳኝ ነው

ድሬዳዋ፣ሐምሌ6/2018 (ኢዜአ)፡-ዲጂታል የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባን ውጤታማ ማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለመቅረጽ ወሳኝ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ገለጸ።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አገልግሎት ጋር በመሆን የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዲጂታል ሲስተምን በድሬዳዋ አስጀምረዋል።


 

በማስጀመሪያ ሥነስርአቱ ላይ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እንደተናገሩት፤ ዲጂታል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት ሥርአትን በተቀናጀ መልኩ መስጠት ተደራሽነትን ያሰፋል።

ዲጂታል የሲቪልና የቤተሰብ ምዝገባን ውጤታማ ማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለመቅረጽ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ዕቅዶችን አውጥቶ አፈጻጸማቸውን ለመከታተል ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለውም አንስተዋል።

የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ ዲጂታል አገልግሎት ለስታስቲክስ መረጃዎች ትንተና እንዲሁም ለፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛ መረጃ  ለመስጠት ወሳኝ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያመለከቱት።


 

የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው በድሬዳዋና አዲስ አበባ አገልግሎቱ  የተጀመረው የሲቪልና ቤተሰብ ዲጂታል አገልግሎት "የዲጂታል 2030"  ትግበራ  አካል መሆኑን አንስተዋል።

ተግባሩ ቀልጣፋ አገልግሎትን ዕውን በማድረግ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በላቀ ውጤት ለመፍታት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

ዲጂታል አገልግሎቱ የልደት፣ የጋብቻ፣ የሞት መረጃዎችን በቴክኖሎጂ በመቀመር ለሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ መሳካት   ለማዋል  በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ዛሬ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ በድሬዳዋ ወደ ተግባር የተሻገረው ዲጂታል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት፣ ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ብልፅግና  ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

የተጀመረውን ዲጂታል አገልግሎት ከመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጋር ተሳስሮ የላቀ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።

በሥነስርዓቱ ላይ የፌደራል እና የድሬዳዋ አስተዳደር ባለስልጣናት፣ የተቋማት አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም