ቀጥታ፡

የኩታገጠም እርሻ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እያፋጠነ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኩታገጠም የግብርና እርሻ ሥርዓት የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እያፋጠነ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥የገጠር ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂው የአርሶ አደሩን የግብርና ሥርዓት በማዘመን፣ዘላቂ የምርታማነት ምኅዳር በመፍጠር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነት አድማስ እየሰፋ መምጣቱ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥና ለገጠር ትራንስፎርሜሽን መፋጠን ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።


 

ይህም የግብርናውን ዘርፍ ከባህላዊ አሠራር በማላቀቅ አዳዲስ አማራጮችን በመፍጠርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የአርሶ አደሩ ተጠቃሚነትና የኑሮ ደረጃ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የኩታገጠም የግብርና አሠራርና የሜካናይዜሽን ሥርዓት መተግበር የሰብል ምርታማነትን በብዛትና በጥራት ለማሳደግ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ይታረስ የነበረው መሬት አሁን ላይ በበጋ መስኖና በተለያዩ የምርታማነት ወቅቶች ታግዞ ምርታማነቱን ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣የሀገሪቱን የምግብ ፍጆታ በማሟላት አልፎም ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚችልበትን አስተማማኝ መዋቅራዊ የስኬት ሽግግር ማስመዝገቡን አብራርተዋል።


 

የኩታገጠም ዘመናዊ አስተራረስ ዘዴም የሚታረስን መሬት በማስፋትና አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያ የሚያቀርብበትን አቅም በመፍጠር የገጠር ኢኮኖሚን እያነቃቃ ነው ብለዋል።

ይህ አሠራር ለግብርና ምርቶች እሴት በመጨመር ረገድ በሚደረጉ ጥረቶች ታግዞ የገጠር ሽግግርን ከማፋጠን ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለኢንዱስትሪ ልማት ግብዓት በማቅረብ ረገድ አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኩታገጠም የግብርና አስተራረስና የሜካናይዜሽን ሥርዓት መዘርጋት የኢትዮጵያን የግብርና ዘርፍ ወደ ዘመናዊ ምዕራፍ በማሸጋገር የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደግ ጉዞን እያፋጠነ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም