ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት በመጠበቅ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር የኃይል ማመንጫ ግድቦች ደህንነት በማስጠበቅና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ ገለጹ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ያለና እስካሁን ባሉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ያስቻለ ነው። 

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ወደ ትግበራ ተገብቷል።


 

መርሐ-ግብሩ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ብሎም ወደ ግድቦች የሚገባውን የደለል ክምችት በመቀነስ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል ነው። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አረንጓዴ አሻራ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል መከላከል ያስችላል። 

በዚህም ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ለውጥ መመዝገቡን ጠቅሰው፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ግድቦች የሚይዙትን የውሃ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ተናግረዋል። 

በዚህም በሀገሪቱ አስተማማኝ እና ዘላቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ለሚከናወነው ተግባር አስተዋጽኦ በማበርከት የኃይል ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። 

ተቋሙም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ላይ በመሳተፍ በሁሉም የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች በንቃት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።


 

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽን እና ኢነርጂ መረጃ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ዳቢ በበኩላቸው፤ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለማረጋገጥ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ደህንነት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል። 

የግድቦችን ደህንነት ማስጠበቅና ከደለል መጠበቅ የሀገሪቱን የኢነርጂ ዋስትና አስተማማኝ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር በዚህ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል። 

ተፋሰሶችን ማዕከል በማድረግ እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብርና የተፋሰስ ልማት ሥራ የኃይል ማመንጫዎችን ደህንነት ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም