ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ገጽታንም በእጅጉ የለወጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ገጽታንም በእጅጉ የለወጡ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ገጽታን በእጅጉ የለወጡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባን የለወጡ እጅግ አስደማሚ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተከናወኑት የልማት ሥራዎች እጅግ ስኬታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋን ወደ ላቀ ደረጃ የለወጡና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአስፈጻሚው አካልና በምክር ቤቱ መካከል የነበረው ግንኙነት እጅግ ጤናማና መልካም የሥራ ባህል የነበረው መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ አዎንታዊ አሠራርና መልካም ባህል በቀጣዩ ምክር ቤትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ትልቅ ተስፋ ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ደብረሲና ሙሴ በበኩላቸው ያለፉት አምስት ዓመታት ለምክር ቤቱ አዲስ የሥራ ምዕራፍና ስኬት የታየበት ወቅት እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህ ጊዜ ውስጥ የተከናወኑት የማህበራዊ ዘርፍ ሥራዎች በግልጽ በአይን የሚታዩና የሕዝብን የኑሮ ፍላጎት በአግባቡ የመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ነባር የጤና ተቋማት እንዲስፋፉና አዳዲስ ዘመናዊ ተቋማት እንዲገነቡ መደረጉ እንዲሁም፤ የትምህርት ተደራሽነትና የተማሪዎች ቅበላ እንዲጨምር ምክር ቤቱ ጠንካራ ግፊት ሲያደርግ መቆየቱንና አስፈጻሚው አካልም በዚህ ልክ የተሻሉ ሥራዎችን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
ምክር ቤቱ የሕዝብ ድምፅ በመሆን ለነዚህ መልካም ሥራዎች ጠንካራ መሠረት መጣሉን የገለጹት አባልዋ ቀጣዩ ምክር ቤትም የተጀመረውን የልማት ጉዞ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
የምክር ቤት አባሉ ኢቲሳ ደሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ያለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች ፈጣን ለውጥ የታየበት ወቅት እንደነበር ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም ዘመናዊ ማሽነሪዎች የተሟሉላቸው ሆስፒታሎች መገንባታቸው ቀድሞ ወደ ውጭ አገር የሚደረጉ የሕክምና ጉዞዎችን እንደሚያስቀርና በትምህርትም ዘርፍ የተማሪዎች ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
የተጀመሩት አበረታች የልማትና የፖለቲካ ስኬቶች ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመሆኑም የሚቀጥለው ምክር ቤት የተጀመሩትን ፈጣን የልማት ሥራዎች በቁርጠኝነት ይዞ መስራትና ህብረተሰቡን በታማኝነት ማገልገል እንዳለበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የምክር ቤት አባሉ አባወይ ዮሐንስ እንደገለጹት ባለፉት አመታት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተወዳዳሪ ከማድረግ አንፃር ማህበረሰቡን መሰረት ያደረጉና የልማት ጥያቄዎችን በተግባር የመለሱ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች ተተግብረዋል።
ነዋሪዎች ቀድሞ ሩቅ ቦታ ሄደው የሚያዩትንና የሚመኙትን ዘመናዊ የከተማ አኗኗር፣ በአካባቢያቸው ማግኘት መቻላቸው የፕሮጀክቶቹን የሕዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በጤና እና በትምህርት ዘርፍ አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።