የገበያ ማዕከላት መስፋፋት የዋጋ ንረትን ለመቀነስና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ወሳኝ መፍትሔ ሆነዋል -ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
የገበያ ማዕከላት መስፋፋት የዋጋ ንረትን ለመቀነስና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ወሳኝ መፍትሔ ሆነዋል -ሸማቾች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የገበያ ማዕከላትና የቅዳሜና እሁድ ገበያ መስፋፋት የዋጋ ንረትን ለመቀነስና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት ወሳኝ መፍትሔ እንደሆኗቸው ሸማቾች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ መንግሥት የኑሮ ውድነትንና ገበያን ለማረጋጋት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት በርካታ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል።
ከተወሰዱ ቀዳሚ እርምጃዎች መካከል የሸማቾችን አማራጭ ማሳደግ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ተደራሽነት ከ2ሺህ በላይ ማድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
የገበያ ማዕከላት የከተማዋን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እንደ ዋነኛ መፍትሔ የሚያገለግሉ ሲሆን እነዚህ ማዕከላት የግብርና ምርቶችን በቀጥታ ከአምራች ወደ ሸማች በማገናኘት፣ በመካከል የሚፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ በመግታት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ ተደራሽ ያደርጋሉ።
ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎትም ከፍ ያለ ነው፤ ነዋሪዎች የተለያዩ የፍጆታ ዕቃዎችን በአንድ ቦታ በመሸመት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ይቆጥባሉ፤ በተለይም በአቅራቢያቸው በመገንባታቸው የትራንስፖርት ወጪን በማስቀረት የኑሮ ጫናን በእጅጉ ያቀላሉ።
ይህም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከመግዛት ባሻገር፣ በገበያ ውስጥ የሚታየውን የዋጋ አለመረጋጋት በመከላከል ለኅብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እፎይታ ይፈጥራል።
አቶ ሄኖክ ተወልደ እና አቶ ረታ አክሊሉን ጨምሮ ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች እንደገለጹት፣ እነዚህ ማዕከላት ተጨማሪ የትራንስፖርት ወጪን በማስቀረት የቤተሰብ ፍጆታዎችን በቀላሉ ለመሸመት ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
የመንግሥትን የገበያ ማረጋጋት ጥረቶችን አድንቀው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ኤልሳ ተሰማ እንደጠቆሙት፣ በምርቶች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ አለመረጋጋት ለመፍታት እነዚህን ማዕከላት ይበልጥ ማጠናከርና ማስፋፋት ይገባል።
መንግሥት ለዚህ ተግባር ልዩ ትኩረት በመስጠት የኑሮ ጫናውን ለማቃለል የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይበልጥ ማጠናክር እንደሚገባው ጠቅሰው ይህን የመሰለ የህዝብ ተጠቃሚነትን ያማከለ ሂደት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት የምርት አቅርቦትን ለመጨመር የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ለመገንባት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው የአቅርቦት ሰንሰለቱን ይበልጥ የማዘመን እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ኃቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡ ልዩ ልዩ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ አምራቾችና አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን በቀጥታ የሚያቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ሥራ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የንግድ ሰንሰለቱን በማናጋት በሸማቹና በአምራቹ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ሕገ-ወጥ ደላሎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ የቁጥጥርና የሕግ ማስከበር ሥርዓት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
መንግሥት በቀጣይም የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና የሚያቃልሉ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡