አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዜጎችን ኢኮኖሚያዉ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዜጎችን ኢኮኖሚያዉ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው
ደብረ ማርቆስ፤ ሃምሌ 6/2018(ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የዜጎችን ኢኮኖሚያዉ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያስቻለ መሆኑን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ገለጹ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የማስጀመሪያ ስነ ስርአት በደጀን ወረዳ በየትኑራ ቀበሌ ዛሬ ተካሂዷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዮ ችግኞች ተሸፍኗል።
በዚሁ ወቅት 10 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 14 ነጥብ ስድስት በመቶ ወደ 18 ነጥብ ዘጠኝ በመቶ ማሳደግ እንዳስቻለም ነው የተናገሩት።
በዘንድሮው የክረምት መርሃ ግብርም አርሶ አደሩን፣ ወጣቶችንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍ የችግኝ ተከላውን ስኬታማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋለ አባተ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የዞኑን ብዝሃ -ሕይወት ከማስጠበቅ ባለፈ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እያስቻለ መሆኑን ይገልፃሉ።
መርሃ ግብሩ ተፋሰሶችን ለመልማት፤የእንስሳት መኖን ለማምረት፤ ለወተትና ከብት ማድለብ ልማት፣ የከርሰ ምድር ውሃ ለማበልፀግ ፣ ለመስኖና ለንብ ማነብ ስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት የአፈር ለምንትን በመመለስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያስቻለ በመሆኑም ለቀጣይነቱ ሁሉም ዜጋ መረባረብ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ እንዳሉት፤ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ለተተኪው ትውልድ የተመቸ አካባቢን ለማውረስ መሰረት የጣለ ተግባር ነው።
በክረምቱ ወቅትም በ33 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ከ264 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
የደጀን ወረዳ የየትኑራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቸሬ ጸጋዬ ፤በየዓመቱ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚነታቸውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እየቻሉ መሆኑን ተናግረዋል።
የችግኝ ተከላው የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማድረግ በንብ ማነብ፣ በመኖና እንስሳት ልማት ዘርፎች ተሳትፈው ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ነው ያረጋገጡት።
የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሞስነህ አድማስ በበኩላቸው ፤በየዓመቱ የሚተክሏቸውን ችግኞች በመንከባከብ ለታለመለት አላማ እንዲውሉ እየሰሩ መሆኑ አስረድተዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።