የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ ነው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሻሻል ውጤት እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የግብርና ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረት የአህጉር-አቀፍ የእንስሳት ሃብት ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ፎረሙ በአፍሪካ የእንስሳት ሃብት ልማትን በማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል፣ አርብቶ አደሮች የተሻለ ገበያ እንዲያገኙና የሀገራትን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
ኢትዮጵያ የእንስሳት ሃብት ልማትን በማሳደግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ እየሰራችበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አርሶና አርብቶ አደሮች የሚያጋጥሟቸውን የውሃና የመኖ እጥረት በዘላቂነት የሚቀርፉ እንዲሁም የእንስሳት ሕክምና መስጫ ተቋማትን የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከአርብቶ አደሮች ጋር የሚሰሩ ተቋማትን፣ የእንስሳት ገበያ ማእከላትን ለአርብቶ አደር አካባቢዎች ተደራሸነት የማጠናከር ስራዎችንም እየተሰራበት እንደሆነም አብራርተዋል።
በአፍሪካ ህብረት የእንስሳት ሀብት ቢሮ ዳይሬክተር ሁያም ሳሊህ (ዶ/ር) አፍሪካ የዓለምን የእንስሳት ሃብት ከፍተኛ ድርሻ ብትይዝም፣ ከእሴቱ ግን የምታገኘው በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል።
በቀጣይም የአህጉሪቷን ግዙፍ የእንስሳት ሃብት በማልማት የአርሶና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማሻሻል በሁሉም ዘርፍ የኢንቨስተመንት አማራጮችን ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።