ቀጥታ፡

የአፍሪካን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የሚያሳልጥ የዲጂታል አቅም መገንባት ያስፈልጋል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦የአፍሪካን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነት የሚያሳልጥ የዲጂታል ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ የአፍሪካ ህብረት ገለጸ። 

የአፍሪካ የትምህርት ፈጠራ ኤክስፖ 2026 በአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

''የትምህርት ዲጂታል ሽግግርና የፈጠራ መፍትሔዎችን ማሳደግ'' በሚል መሪ ሃሳብ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ኤክስፖ የፈጠራ ባለቤቶች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ጋስፓርድ ባንያን ክምቢና በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ብቁ የሰው ሃይል መገንባት ያስፈልጋል።

ለዚህም በአፍሪካ ሕብረት በተገባው የፖለቲካ ቁርጠኝነት መሰረት አፍሪካዊያን በተለወጠ ዓለም ውስጥ የትውልዱን ዕውቀትና ክህሎት ለማዳበር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአፍሪካን ትምህርት ወደ ዲጂታል ማሸጋገር ወቅታዊ እና የሀገራትን ትኩረት የሚፈልግ ነው ብለዋል።  

በአፍሪካ አካታች የዲጂታል ትምህርት ስርአት በመዘርጋት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ፣ የዲጂታል የትምህርት ግብዓቶችን ማሟላት ላይም ይበልጥ መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ትምህርትን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተቃኘ ማድረግ እና የአስተማሪዎችን የቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ ትምህርትን ለማሸጋገር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል።   

የጥናትና ምርምር ተቋማትን አቅም ማሳደግም የሀገራት የትኩረት ማዕከል ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ህብረትም በአህጉሪቱ ትምህርትን ለማዘመን የሚሰሩ ተግባራትን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም