በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የተተገበሩ አሰራሮች ውጤት አስገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ የተተገበሩ አሰራሮች ውጤት አስገኝተዋል
አዳማ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ በግብርና ዘርፍ የተተገበሩ አሰራሮች ውጤት ማስገኘታቸውን የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አብዲ ያዩ (ዶ/ር) ገለፁ።
የክልሉ የመንግሥትና የፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ይገኛል።
በግምገማው መድረክ ላይ ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡት የክልሉ ፕላንና ልማት ኮሚሽነር አብዲ ያዩ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ የተተገበሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና የተደረጉ ሁለንተናዊ ድጋፎች ከፍተኛ ውጤት አስገኝተዋል።
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በከተሞችና በገጠር አካባቢዎች የወተት ላሞች እርባታ በዘመናዊ መንገድ መተግበሩና ምርጥ የእርባታ ዶሮዎች ለአርሶ አደሩ መሰራጨታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በዓሣ እርባታ ዘርፍ ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የዓሣ ጫጩቶች ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ተሰራጭተው ወደ እርባታ ኩሬዎች መግባታቸውን ገልጸዋል።
የአርሶ አደሩን የሰብል ልማት ውጤታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና በቅርበት የገበያ ትስስር የሚያገኝበት ምቹ የገበያ ማዕከላት መገንባታቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል።
ይህም የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደጉ ባለፈ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ትልቅ እገዛ ማድረጉን አስረድተዋል።
በክልሉ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ በተደረገው ሰፊ ጥረትም በበጀት ዓመቱ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት በራስ አቅም ለመሸፈን በተደረገው የውስጥ ገቢ ማሰባሰብ ጥረትም የተሻለ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት 13 ሺህ 147 አዳዲስ አልሚ ባለሀብቶችን መሳብ ተችሏል ነው ያሉት።
ይህንን ተግባር ይበልጥ ለማስቀጠልም አርሶ አደሮችና የአገር ውስጥ አንቀሳቃሾችን በመደገፍ፣ ሀብት አፍርተው ከእርሻ ሥራ ወደ ኢንቨስትመንት ባለቤትነት እንዲሻገሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የሕዝቡን የማኅበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረትም በትምህርት፣ በጤና፣ በንጹህ መጠጥ ውኃና በመንገድ ልማት ዘርፎች እጅግ የተሻለና አበረታች አፈጻጸም መመዝገቡን አንስተዋል።
በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ያለው ይህ የመንግሥትና የፓርቲ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ በቀጣዮቹ ቀናትም እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።