በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል
ሳውላ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የመማር ማስተማር ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ "ትምህርት ለልጄ" በሚል መሪ ሃሳብ የ2018 ዓ.ም የክረምት ትምህርት ንቅናቄ መድረክ በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፣ ባለፉት ዓመታት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና ግብአት በማሟላት ተማሪዎች ብቁ ሆነው እንዲወጡ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸው፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና ምቹ በማድረግ የመማር ማስተማር ስራውን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልጸው፣ ጥራቱን የጠበቀና ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ውጤት ማሻሻል ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል።
የዛሬው የ"ትምህርት ለልጄ" ንቅናቄም ተማሪዎች የክረምት ወራትን ካላስፈላጊ ቦታ ይልቅ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያሳልፉ ስለሚያግዝ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቢሮው ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሁሉም አካባቢዎች በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በየአመቱ የሚካሄደው የትምህርት ንቅናቄ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተስተዋለውን የውጤት ማሽቆልቆልና የጥራት ችግር ለመፍታት በተሰራው ሥራ የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል በቀጣይም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በክረምት ወራት በጎ ፈቃደኛ ወጣት መምህራንን እና የማህበረሰቡን አቅም በመጠቀም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እና ግብዓት ለማሟላት በቅንጅት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
በዞኑ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን በብቃት ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ፍትሃዊ የትምህርት ተደራሽነት መረጋገጡን አንስተው፣ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ፣ የዞን እና የከተማ አስተዳደር የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።