ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ውጤታማ ስራ ተሰርቷል

ሐረር፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነ የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ውጤታማ ስራ መሰራቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ በትምህርት ዘርፍ በተሰሩ ሥራዎች ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል። 

ትምህርት ከታች መሠረት ካልተሠራለት የላይኛው ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለመዋዕለ ሕፃናት ማስፋፊያ በተሰጠው ልዩ ትኩረት 35 ሺህ መዋዕለ ሕፃናትን መገንባት መቻሉን ጠቅሰዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አርሰላን አብዲ፤ በሐረሪ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነ የትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በዚህም በሕዝብ ንቅናቄና በትምህርት ባለሙያዎች የተቀናጀ ሥራ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ፣ ተሳትፎን ከማጎልበትና የተማሪዎችን ውጤት ከማሻሻል አኳያ የተሻለ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም በክልሉ በበጀት ዓመቱ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ልማት ላይ በተከናወነው ሥራ በሁሉም የከተማና የገጠር አካባቢዎች በሚገኙ 69 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የቅድመ መደበኛ ትምህርት መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶቹም የትምህርት ማቋረጥ እንዳይከሰት ለማድረግ፣ በሁሉም ቅድመ መደበኛ እና ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም መከናወኑን አስታውቀዋል።

በ2019 የትምህርት ዘመን ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፤ ለዚህም በክልሉ ገጠር ወረዳዎች 6 አዳዲስ  የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

በክልሉ በ“ትምህርት ለትውልድ” መርሃ ግብር የሚከናወኑ ሥራዎች የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በማስቻል ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት በገንዘብ፣ በዓይነትና በዕውቀት 38 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሥራ መሰራቱን ገልጸው፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ደግሞ ከ 42 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል። 

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የሚከናወኑ ሁሉን አቀፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ምክትል ቢሮ ኃላፊው አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም