ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሯል

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ስራ መከናወኑን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ገለፀ።

በክልሉ ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚያገለግሉ ፀጋዎችን በመለየት ለወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማሳደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል።

የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዳርጋቸው ጎፋ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ለመፍጠር ተችሏል።


 

በዚሁ ወቅት የስራ እድል ፈጠራዉን ስኬታማ ለማድረግ  በቅንጅት የሚመራ ግብረ ኃይል በማቋቋም እና አጋር ተቋማትን በማቀናጀት ሰፊ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል።

ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥም 75 በመቶ በቋሚነት የተፈጠረ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 50 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

የስራ ዕድሉ በመስኖ እና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በጨርቃጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በእንጨትና ብረታብረት ስራዎች የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ ወቅት በስራ እድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች የገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማቸው ለማድረግ በተከናወኑት ተግባራትም  7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር  ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።


 

በተጨማሪም 21 ሺህ 400 ሄክታር የሚጠጋ መሬትና ከ 2 ሺህ 200 የሚበልጡ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶች ተገንብተው የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች ማስተላለፍ መቻሉን ገልፀዋል።

ኢንተርፕራይዞቹ የገበያ ትስስር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተከናወኑት ተግባራትም የ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን የሀገር ውስጥ፤ ከ1 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ሃገራት የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም