ቀጥታ፡

ዜጎችን ከሰቀቀን ኑሮ ወደ አዲስ ህይወት እያመጣ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 

ሰቆጣ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ በጎነት የራስን፣ የቤተሰብንና የማኅበረሰብን አቅምና ዕውቀት አስተባብሮ በችግር ውስጥ የሚኖሩ ወገኖችን በመደገፍ ወደ አዲስ ሕይወት ማሸጋገር ነው።

ማኅበረሰቡ ለዘመናት በአካባቢው የሚኖሩ አቅመ ደካሞችን በማብላት፣ በማጠጣትና የፈረሱ ቤቶቻቸውን በማደስ ተደስተው እንዲኖሩ የሚያደርገውን ይህንን መልካም እሴት በትውልድ ቅብብሎሽ አጠናክሮ ያስቀጥልበታል። 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ልዩ ትኩረት የተሰጠው የበጎነት ተግባር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ሁሉም ዜጋ የሚሳተፍበትና ወገኖችን ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ንቅናቄ ሆኗል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአስ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ብርሃኔ ወንድማገኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑና ቤት ተከራይቶ ለመኖር አቅም በማጣታቸው፣ ከጎዳና ሕይወት ባልተናነሰ ሁኔታ በፈራረሰ ጎጆ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ።

"መኖሪያ ቤቴ ክረምት በመጣ ቁጥር ስለሚያፈስ ከሁለት ልጆቼ ጋር በዝናብ፣ በውርጭና በቁር እየተሰቃየን እናሳልፍ ነበር፤ በተለይ ዝናብ ሲዘንብ ወደ አንድ ጥግ ተሰብስበን በመጠለል ነበር የምናሳልፈው" ይላሉ።

ችግሩን የተገነዘቡት የከተማዋ በጎ ፈቃደኞች ለአቅመ ደካሞች አዲስ መኖሪያ ቤት ገንብተው ሲያስረክቡ የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ወይዘሮ ብርሃኔ አሁን ላይ ክረምት ቢመጣ ቢሄድ ምንም ዓይነት ሰቀቀን እንደሌለባቸውና ከነቤተሰቦቻቸው በሰላም ተኝተው፣ ጠዋት በደስታ በመንቃት ወደ ዕለት ተግባራቸው እንደሚሰማሩ ተናግረዋል።

የዚሁ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አድና ደሴ በበኩላቸው፤ የአይን ብርሃናቸውን በተፈጥሮ በማጣታቸው ተንቀሳቅሰው ለመስራትና ሀብት ለማፍራት ባለመቻላቸው ለተደራራቢ ችግሮች ተጋልጠው መኖራቸውን አውስተዋል። 

በደሳሳ ጎጆዋቸው ከልጆቻቸው ጋር በመኖር በክረምት በዝናብ፣ በውርጭና በቁር፤ በበጋ ደግሞ በፀሐይና በነፋስ ይሰቃዩ እንደነበር አስታውሰው፣ በዘንድሮው ዓመት በበጎ ፈቃደኞች በተደረገላቸው ድጋፍ አሁን ላይ የተሻለ ሕይወት መምራት እንደቻሉ ገልጸዋል።

በአስ ከተማ በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሀብቱ ሰለሞን፤ የከተማዋን ነዋሪ በማስተባበር በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን አኗኗር ለመቀየር ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጿል። 

በከተማዋ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ባለፉት ዓመታት የአቅመ ደካማ ዜጎችን ቤቶች በመገንባትና በማደስ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ማድረጋቸውንም አመልክቷል።

በአስተዳደሩ የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበባው ደሳለኝ እንዳሉት፤ በወረዳው በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር 14 አዳዲስ ቤቶች ተገንብተው ለአቅመ ደካሞች ለማስረከብ ተችሏል። 

ከተገነቡት መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሦስቱ በበጋው ወቅት በተካሄደው የበጎ ፈቃድ ሥራ ተገንብተው የተጠናቀቁ ሲሆን፣ የክረምቱ ወቅት ከመግባቱ በፊት ለአቅመ ደካሞች ማስተላለፍ መቻሉን ገልጸዋል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የዜጎች በጎ ፈቃድ አገልግሎትና የወጣቶች ንቅናቄ ተሳትፎ ቡድን መሪ አቶ ሙሉጌታ ስኳር እንዳሉት፤ በዘንድሮው የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 197 ሺህ 250 ወጣቶች ይሳተፋሉ። 

በዚህ መርሐግብር 584 ሺህ 860 የሚሆኑ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በትጋት እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም