የሌማት ትሩፋት ሀገራዊ ስኬት- ከአመጋገብ ለውጥ እስከ ገቢ ምንጭ - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት ሀገራዊ ስኬት- ከአመጋገብ ለውጥ እስከ ገቢ ምንጭ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦ለብዙ ኢትዮጵያውያን ወተት፣ እንቁላል፣ ማርና ሥጋ በምግብ ገበታ የማይገኙ፣ ለረጅም ዓመታት የቅንጦት ያህል የሚታዩና በቂ ምርት ባለመኖሩም በገበያ ላይ በስፋት የማይገኙ ነበሩ።
ይህንን እውነታ ለመቀየርና የዜጎችን የሥርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የሌማት ትሩፋት ሀገራዊ መርሃ ግብር ዛሬ ላይ ትልቅ ተስፋና ተጨባጭ ውጤት እያሳየ ይገኛል።
ቀደም ሲል ትኩረት አጥቶ የነበረውን የእንስሳት ተዋጽኦ ልማት በቅንጅትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ረገድ በአካባቢው ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
በግብርና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት መርሃ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት የነበረው 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት ዘንድሮ 15 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር መድረሱ፣ በዓመት የሚሰራጨው የዶሮ ጫጩት ከ26 ሚሊዮን ወደ 184 ሚሊዮን ማደጉ እንዲሁም የእንቁላል ምርት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ከፍ ማለቱ የዚሁ ሀገራዊ ስኬት ማሳያዎች ናቸው።
ይህ የተጀመረው አበረታች ሂደት እንደ ወተት፣ ማር፣ ሥጋ፣ አሳ እና እንቁላል ያሉ ምርቶች የቅንጦት ሳይሆኑ የዜጎች የዕለት ተዕለት የሥርዓተ ምግብ አካል እንዲሆኑ በማስቻል ረገድም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
መርሐግብሩ በቢሾፍቱ ከተማና አካባቢዋ ለሚኖሩ በርካታ ዜጎችም የአመጋገብ ሥርዓትን ከመቀየር ባለፈ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን የለወጠ የሕይወት ጉዞን ፈጥሮላቸዋል።
አቶ ከፈለኝ ጫላ ቀደም ሲል በመንግሥት ሥራ በደመወዝ ነበር የሚተዳደሩት። የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ላይ ዜጎች እንዲሳተፉ ጥሪ ሲቀርብ ግን የቀደማቸው አልነበረም።
ገንዘብ በብድር በማመቻቸት በአንድ የወተት ላም ሥራቸውን ጀመሩ። በአሁኑ ወቅት የወተት ላሞቻቸውን ቁጥር 15 ማድረስ ችለዋል።
የአካባቢው አስተዳደርና ባለሙያዎች ያደረጉላቸው ተከታታይ ድጋፍና ክትትል አሁን ለደረሱበት ውጤት እንዲበቁ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ያነሳሉ አቶ ከፈለኝ።
የራሳቸውን ኑሮ ከመቀየር ባለፈ፣ የሚያመርቱትን ወተት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን በማረጋጋት ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
የተመጣጠነ አመጋገብን እንድንከተል የሌማት ትሩፋት ትልቅ ለውጥ አምጥቷል የሚሉት አቶ ከፈለኝ፥ በተጨማሪም በመስኩ ለሌሎች ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው በዚሁ መርሃ ግብር ሕይወታቸው የተቀየረው ሥራ ፈጣሪ አቶ ጌቱ ብሩ ናቸው። እሳቸው ደግሞ በተቀናጀ የዶሮና የዓሣ ልማት ዘርፍ ላይ ነው የተሰማሩት።
የሌማት ትሩፋት ያመጣላቸው በረከት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመጥቀም አልፎ የንግድ አድማሳቸውን አስፍቶላቸዋል።
ከልማቱ በሚያገኙት የምርት ውጤት የራሳቸውን ሆቴል መክፈት የቻሉ ሲሆን፣ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
"ለሆቴላችን የምግብ ግብዓት የሚሆነውን ምርት የምናቀርበው ከራሳችን የዶሮና የዓሣ እርባታ ማዕከል ነው" የሚሉት አቶ ጌቱ፣ ዘርፉ ሰፊና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት መሆኑን ይመሰክራሉ።
አቶ ጌቱ እቅዳቸው እዚህ ላይ ብቻ አያበቃም፤ በቀጣይ የሌማት ትሩፋት ምርቶችን እሴት ጨምረው ለከተሞች ከማቅረብ ባለፈ ወደ ውጭ ሀገር ለመላክና ለሀገር የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ውጥን አላቸው።
ሌሎችም በዚህ ሥራ ላይ ቢሰማሩ ከራሳቸው አልፈው ሀገርንና ወገንን መለወጥ እንደሚችሉም ነው የጠቆሙት።
በተመሳሳይ በዶሮ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ደረጄ አበበ መርሃ ግብሩ ከፍተኛ ገቢ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
የዶሮ እንቁላል በተመጣጣኝ ዋጋ ለአካባቢው ማኅበረሰብ በስፋት በማቅረብ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር)፥ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበትና የዜጎችን የምግብና ሥርዓተ ምግብ አቅም እያሳደገ የሚገኝ ኢኒሼቲቭ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ሀገራዊ ጥረት ለማሳካት የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አክለውም፤ ኢኒሼቲቩ በቤተሰብ ደረጃ የዶሮ እርባታ ባህል እንዲሆን በማድረግ፣ በተለይም ሕፃናትና እናቶች የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑንና ምርቶች በስፋት ለገበያ እንዲቀርቡ በማስቻል ረገድ ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።