ቀጥታ፡

በሀረሪ ክልል ወቅቱን የዋጀ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ) ፦ በሀረሪ ክልል ወቅቱን የዋጀ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ተግባራትን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲል የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ሔኖክ ሙሉነህ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት በሰጡት መግለጫ መረጃን ለማህበረሰቡ ከማድረስ ባለፈ የአፍራሽ ሀይሉን አጀንዳ በማምከን ረገድ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ጽሕፈት ቤቱ በክልሉ በ2018 የበጀት ዓመት ወቅቱን የዋጀ የኮሙኒኬሽንና የሚዲያ ተግባራትን ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።

የክልሉ ህዝብ በሰላም፣ በመቻቻልና በአብሮነት የመኖር እሴቶች እንዲጠናከር እንዲሁሞ በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦች እንዲተዋወቁ በማድረግ ረገድ የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም የተጠናከረ ስራ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

የክልሉን መልካም ገፅታ በመገንባት በህዝብና በመንግስት መካከል ሁነኛ የመረጃ ድልድይ ሆኖ ተግባቦትን የመፍጠር ስራዎችም በትኩረት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አስረድተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የሚከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎችን በማህበራዊ ሚዲያና በአካባቢው የሚገኙ ሀገር አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም ለህዝቡ ተደራሽ ተደርጓል ብለዋል።

አቶ ሔኖክ አክለውም በተለይም በክልላዊና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማጎልበት ያስቻሉ ስራዎችም ትኩረት ተሰጥቶት መሰራቱን ጠቁመዋል።

የጋራ መግባባት በመፍጠር ረገድም የኮሙዩኒኬሽን ዘርፉ የድርሻውን እንዲወጣ ለማስቻል ጥረት ስለመደረጉም አስረድተዋል።

በአዲሱ የበጀት አመትም ጽሕፈት ቤቱ የህብረተሰቡን የመረጃ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እንደሚሰራ ነው ኃላፊው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም