በኦሮሚያ ክልል የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት ያስቻሉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት ያስቻሉ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል
አዳማ፤ ሐምሌ 6/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች መፍታት ያስቻሉ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የኦሮሚያ ክልል የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ ሕዝብ ሲነሱ የነበሩ የልማት ጥያቄዎች በተጨባጭ ምላሽ አግኝተዋል ብለዋል።
በተለይም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም ዘርፎች ስኬታማ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸው፤ በዚህ ሂደት አመራሩ የክልሉን ሰላም በማረጋገጥ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች እንዲሳለጡ አድርጓል ነው ያሉት።
የመንግሥትን በጀት እና የሕዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት የሕዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የተደረገው ርብርብ ውጤታማ እንደነበርም አንስተዋል።
ይህም በመሆኑ የክልሉ አመራር የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ስልቶችን መፈተሽና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ቀጣይ ሥራዎች መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።
በቀጣዩ በጀት ዓመትም በክልሉ ካለው እምቅ አቅምና የልማት ፍላጎት ጋር የሚጣጣም የተለጠጠ ዕቅድ በማዘጋጀት፣ ያሉትን አማራጮች አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተለይም የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በቁጠባ ላይ በትኩረት መሥራት የሚገባ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳለጥ በዞኖች፣ በወረዳዎችና በከተሞች ያሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፈተሽና ሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ያለው የአመራርነት አቅምና ብቃት በግምገማው በመፈተሽ በተገኙ ውስን ድሎች ሳይዘናጉ አሁንም በሙሉ አቅም መረባረብ ይገባልም ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ተስፋ ሰጪ ድሎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ 21 ሺህ የሚጠጉ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቁ መደረጉን አንስተው፤ ይህም የዓመቱን ዕቅድ አፈጻጸም ውጤታማ ቢያደርገውም፣ አፈጻጸሙ በሁሉም ዞኖችና ከተሞች ወጥነት ያለው አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ በመውጣት ለዴሞክራሲ ያለውን ፅኑ ፍላጎት ያሳየበትና ትልቅ የፖለቲካ ድል የተመዘገበበት መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ፤ በተያዘው አዲሱ የበጀት ዓመት አመራሩ በሙሉ አቅሙና ቁርጠኝነት መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።