የአዲስ አበባ ማህበራዊ ልማት ስኬቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ማህበራዊ ልማት ስኬቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ ናቸው
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ልማት ስኬቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስቻሉ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እናደርጋታለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ መሠረታዊና ሥር ነቀል ለውጦችን ማከናወናችንን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሥር የሰደዱ ኋላቀር አስተሳሰቦችንና ችግሮችን በጽናት በመጋፈጥ፣ አዲስ አበባን ከማይጠቅም የመሳሳብና የመገፋፋት ፖለቲካ የተላቀቀች የሰላምና የልማት ማዕከል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመገንባት አሰባሳቢና የወል ትርክት ለማስረጽ የሚያስችሉ መሠረቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ ውብ፣ አረንጓዴና ጽዱ በመሆን ለኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን የሚያስችሉ መሠረቶችን እየጣለች እንደምትገኝ አስረድተዋል።
የመዲናዋን ጎስቋላ ገጽታ በመቀየር ከተማዋ ከአፍሪካ አስር ጽዱ ከተሞች አንዷ በመሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቷን አንስተዋል።
የመዲናዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱም ሌላው የመሠረታዊ ለውጥ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ መንገዶቿ ሰፊ፣ የነበረችበት የጨለማ ገጽታም ወደ ብርሃን መቀየሩን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ይህም ከተማዋ በርካታ ኮንፈረንሶችንና ጎብኝዎችን የማስተናገድ ብቃቷን እንዳሳደገው አብራርተዋል።
የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷም ይበልጥ ጎልብቶ፣ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያን ዋና ከተማችን ብለው የሚጠሯትና የሁላችንም ኩራት መሆኗን ገልጸዋል።
በትምህርት ዘርፍ ማብራሪያቸውም፤ በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ፣ በዕውቀትና በክህሎት የበለጸገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት የሚያስችል መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማዋ የተማሪዎች ቁጥር ከነበረበት 829 ሺህ 158 ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።
የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናዎች እንዲሁም የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ ፈተና የተማሪዎች ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።
በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርም አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ በማድረግ፣ ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት የሚያደርጉበት ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።
የምገባ መርሃ ግብሩም ለተማሪዎች ከሰጠው እፎይታ በተጨማሪ፣ በርካታ እናቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እንዳስቻለም ከንቲባዋ አክለው ገልጸዋል።
በሌላ መልኩም አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይ ባለፉት አምስት ዓመታት በጤናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ እመርታዊ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
ይህ ጥረት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማሳደግ፣ የእናቶችና የጨቅላ ሕፃናትን የሞት ምጣኔ ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከሀገር አቀፍ መመዘኛዎች በላይ በመቀነስ ስኬታማ ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል።
በአበበች ጎበና፣ ላፍቶ፣ ኮልፌ እና ገላን ድንገተኛ ሆስፒታሎች ግንባታ እንዲሁም የዳግማዊ ምኒልክና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች ማስፋፊያ፣ ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎቱን በእጅጉ ማሻሻሉን ጠቁመዋል።
በማኅበራዊ ፍትሕ አፈጻጸም ረገድ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ነዋሪዎችን በጤና መድህን በማቀፍ፣ በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም በዳግማዊ ምኒልክ እና ዘውዲቱ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ታካሚዎች በነጻ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ በዓመት እስከ 100 ሚሊዮን ብር ድጎማ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በመዲናዋ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ዘመናዊ የፍሳሽ አወጋገድና ማጣራት ሥርዓትንም መዘርጋት መቻሉን አንስተዋል።