ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድነትን በማጠናከር ማህበራዊ ችግሮችን በተባበረ ክንድ ለማቃለል እያገዘ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አንድነትን በማጠናከር ማህበራዊ ችግሮችን በተባበረ ክንድ ለማቃለል እያገዘ ነው
ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 5/2018(ኢዜአ):-ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባር ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ማህበራዊ ችግሮችን በተባበረ ክንድ ለማቃለል እያገዘ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡ ወጣቶች ዛሬ በድሬዳዋ ሐርላ የገጠር ቀበሌ ለአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ በመቆፈር አዘጋጅተዋል።
በስነሥርአቱ ላይ የተሳተፉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ ወጣት እንደገና ፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጸው፤ ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶቹ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማሳካት በትጋት እየሰሩ ነው።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ወጣቶች ውጤታማ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ለመከወን የ5ተኛ ዙር ዘመቻ መጀመራቸውን ጠቅሶ፣ በምስራቅ የአገሪቱ ክፍልም ከአፋር ቀጥሎ ዛሬ በድሬዳዋ ተገኝተው የተለያዩ በጎ ተግባራትን ማከናወን ጀምረዋል ብሏል።
ወጣቶቹ በሐረላ የገጠር ቀበሌ ለችግኝ መትከያ ጉድጓዶችን ከማዘጋጀት ባለፈ በነገው ዕለትም የከተማ ጽዳት እና አዛውንቶችን የመንከባከብ ሥራ እንደሚያከናውኑ ነው ያስታወቀው።
እንደ ወጣት እንደገና ገለፃ ባለፉት ዓመታት በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች የተከናወኑ ተግባራት ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ከማጠናከር ባለፈ ማህበራዊ ችግሮችን በተባበረ ክንድ ለማቃለል እያገዘ ነው።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች የተወጣጡት የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች በበኩላቸው እንዳሉት መርሀግብሩ የርስ በርስ ግንኙነትን እንዲጎለብትና በጎ ማድረግ ባህል እንዲሆን እያስቻለ ነው።
ከሶማሌ እና ከአፋር ክልሎች የመጡት ወጣት ካልዴይ ሼህ አብዱረህማን እና ወጣት ሁሴን ሁመድ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ ወጣቶች በአብሮነት ተሳትፈው ታላቋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በተጀመረው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ አጋጣሚ ፈጥሯል።
ዛሬ በድሬዳዋ ተገኝተው በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፋቸው የአካባቢውን ማህበረሰብ አናኗር፣ ባህልና ትስስር ለማወቅ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ተግባራትን በማከናወናቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ ከሲዳማ ክልል እና ከአማራ ክልል የመጡት ወጣት ሜሮን ሽመልስ እና ወጣት ሰአዳ ኢንድሪስ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ በሐር አብደላ ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለሀገራዊ አንድነት መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሯ ገለጻ፣ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በድሬዳዋ ማህበራዊ ችግሮችን የሚፈቱ 14 አይነት የበጎ ፈቃድ ልማቶች የሚከናወኑ ሲሆን ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች የተሳተፉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አንዱ ነው።
ወጣቶቹ ዛሬና ነገ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ለድሬዳዋ ወጣቶች ትልቅ መነቃቃት የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።