ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን ገቢ የመሰብሰብ አቅም ተፈጥሯል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የመዲናዋን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን የ350 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ የሚያስችል አቅም መገንባቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።


 

በኢኮኖሚ ጉዳዮች የሪፖርት ማብረሪያቸው፤ መዲናዋ ከአፍሪካ ስድስት ታላላቅ ከተሞች ጋር በተደረገ ዝርዝር ጥናት፣ በበጀት አጠቃቀምና ለዘላቂ ልማት በማዋል ረገድ ቀዳሚ ሆና መመረጧን ገልጸዋል።

በዚህም መሠረት በ2013 በጀት ዓመት 51 ቢሊዮን ብር የነበረው የከተማዋ ገቢ በ2018 በጀት ዓመት ወደ 350 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስታውቀዋል። 

በበጀት ዓመቱም ለመሰብሰብ በዕቅድ የተያዘውን ግብ 100 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ አስረድተዋል።

የዘንድሮው የገቢ አሰባሰብ ከ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ116 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ እና የ50 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡን በሪፖርቱ አመላክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ የገቢ አቅሙን ለማሳደግም የፍትሐዊነት መርህን በተከተለ መልኩ እንዲሰበሰብ በሰፊው መሠራቱን አስረድተዋል።

በኢንቨስትመንት ዘርፍም፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የአዲስ አበባን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅና በማስፋፋት ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ለ22 ሺህ 190 አልሚ ባለሀብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት፣ ለ1,632 ነባር ባለሀብቶች ደግሞ የማስፋፊያ ፈቃድ መስጠት መቻሉን አስታውቀዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው ውስጥ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑት ወደ ሥራ በመግባት ከ54 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በከተማዋ ኢኮኖሚ ውስጥ በማንቀሳቀስ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በመንግሥትና በግል አጋርነት በተቀረጹ የተለያዩ የልማት ዘርፎችና ፕሮጀክቶችም፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከ1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር በላይ የካፒታል ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን አስታውቀዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሀብት ፍሰትና የልማት መነቃቃትና የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃና ፍጥነት በማሳደግ፣ በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል።

በገበያ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነት ቅነሳም፤ በመዲናዋ የኅብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን የሚያሳልጡ ስትራቴጂክ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል። 

በዚህም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ፣ የ8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት ድጎማ በማድረግ ውጤታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በ15 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ የምርት ማከማቻ፣ የጅምላና የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችን ያካተቱ ሰባት ዘመናዊ የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቁመዋል። 

የአማራጭ ገበያ ተደራሽነትን ለማስፋፋት ባለፉት አምስት ዓመታት የተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ገበያ፣ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ወደ 259 ማሳደግ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

በሌማት ትሩፋትና በከተማ ግብርና መርሃ ግብር አማካኝነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት የምግብ ፍጆታቸውን በራሳቸው የማሟላት አቅም እንዲኖራቸው እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

አዲስ አበባ ከ60 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ታሪካዊ የመሠረተ ልማት አብዮት ማካሄዷን አስረድተዋል።

የንግድ አገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና በዘርፉ የሚስተዋሉ ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችን ለመቀየር ባከናወናቸው የተቀናጁ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 'አዲስ መሶብ' ዲጂታል ማዕከላት 99 በመቶ የተገልጋይ እርካታ ማስመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም