የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርት ሉዊስ የጀመረው የቀጥታ በረራ በኢትዮጵያ እና በሞሪሸስ መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርት ሉዊስ የጀመረው የቀጥታ በረራ በኢትዮጵያ እና በሞሪሸስ መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናክራል
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፖርት ሉዊስ የጀመረው የቀጥታ በረራ በኢትዮጵያ እና በሞሪሸስ መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ በመነሳት የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ ወደ ሞሪሽስ በሰር ሲውሳጉር ራምጉላም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
በሥነ ስርዓቱ ላይ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢቪዬሽን የሥራ አስፈፃሚዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የሕዝብ ተወካዮች በአውሮፕላን ማረፊያው ተገኝተዋል።
የበረራው መጀመርም በኢትዮጵያ እና በሞሪሸስ መካከል በቱሪዝም፣በንግድ፣ እና ኢንቨስትመንት እና በኢኮኖሚ መስኮች ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተገልጿል።
በዚህም አዳዲስ የትብብር ዕድሎች መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም ተመላክቷል።
ይህ አዲሱ ቀጥታ በረራ በየሳምንቱ እሮብ፣ አርብ እና እሁድ በሳምንት ሦስት ቀናት የሚከናወን ሲሆን፤ የጉዞ ጊዜን በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱም በላይ መንገደኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ ማዕከል በኩል ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራትና የተቀረው የዓለም ክፍሎች ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲገናኙ ያስችላል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ለማ ያደቻ በዚሁ ወቅት፤ በኢትዮጵያና ሞሪሸስ መካከል አዲሱን ቀጥታ በረራ ለመጀመር በመቻሉ አየር መንገዱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ተናግረዋል።
በረራው በሀገራቱ የንግድ ተቋማት መካከል ያለውን አጋርነት ከማጠናከር ባሻገር፣ በቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንት እና የንግድ ልውውጥ ይበልጥ በማሳደግ ረገድ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን በውስጧ ካሉ ሀገራትና ከተቀረው ዓለም ጋር ለማገናኘት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሞሪሸስ የቱሪዝም ሚኒስትር ክርስቲያን ሃሮልድ ሪቻርድ ዱቫል በበኩላቸው፤ የበረራው መጀመር በአፍሪካ የቱሪዝምና የትስስር ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ቀጥታ በረራ ለቱሪዝም አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚከፍት፣ የኢኮኖሚ ትብብርን እንደሚያጠናክር እና የአፍሪካ ሀገራትን ይበልጥ እንደሚያቀራርብም አክለዋል።