ቀጥታ፡

ኮሌጆቹ በእውቀትና በክህሎት የበቁ መምህራንን ለማፍራት የጀመሩትን ሥራ ያጠናክራሉ

ጎንደር፣ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የሚገኙ የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆች በእውቀትና በክህሎት የበቁ መምህራንን በማፍራት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የጀመሩት ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። 

የጎንደር መምህራን ኮሌጅ በተለያዩ የትምርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 574 እጩ መምህራን ዛሬ አስመርቋል።


 

 በምረቃው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በቢሮው የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደግሰው መለሰ እንደገለጹት፣ በክልሉ የሚገኙ 10 የመምህራን ኮሌጆችን ለማጠናከር በግብአትና በቴክኖሎጂ የመደገፍ ሥራ እየተሰራ ነው።

ኮሌጆቹን ከዘመኑ ጋር ተራማጅ ለማድረግ በየጊዜው የበጀት ማሻሻያ ከማድረግ ባለፈ የመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ የሚገኙ የትምህርት ኮሎጆች ብቁ መምህራንን በማፍራት የትምህርት ስብራትን ለመጠገን እየሰሩት ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል። 

የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ዛሬ ያስመረቃቸው እጩ መምህራን ትውልድን በእውቀት ከማነጽ ሥራቸው ጎን ለጎን ለክልሉ ዘላቂ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።  


 

የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ዲን አቶ ሻንበል ፀሐይ በበኩላቸው እንዳሉት ኮሌጁ ላለፉት 44 ዓመታት ብቃት ያላቸው መምህራንን በማሰልጠን ለአገሪቱ እድገት የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል። 

በዛሬው እለትም 574 እጩ መምህራንን በመጀመሪያ ዲግሪ እና በዲፕሎማ መርሐ ግብሮች አሰልጥኖ ማስመረቁን ተናግረዋል።

መምህራኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና እንደወሰዱ ጠቁመው፣ ከተፈተኑት ውስጥም 87 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት በመጀመሪያው ፈተና የማለፊያ ውጤት አግኝተዋል ብለዋል።

የዛሬው ምሩቃንም የትምህርት ጥራት፣ ተደራሽነትና አግባብነት ችግርን ለመፍታት በተነሳሽነት መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ ናቸው። 


 

ለሥራ በሚመደቡበት አካባቢ የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግና እሴት በመጠበቅ ለሀገር እድገት መሰረት የሚሆን ትውልድ ማነጽ ላይ በትኩረት መስራት ይጠብቅባችኋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

 በዕለቱ 3 ነጥብ 99 ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ ዮሐንስ ሲሳይ፣ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቅት ተጠቅሞ የነገ አገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል።


 

 የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ከ67 ሺህ በላይ መምህራንን በማሰልጠን በሀገር እድገት ላይ  የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ መቆየቱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም