ቀጥታ፡

'' ጀፎረ '' ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር መተሳሳሩ የአርሶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ አድርጓል

ወልቂጤ፤ ሀምሌ 5/2018 (ኢዜአ)--'' ጀፎረ '' ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር መተሳሰሩ የአርሶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እያሳለጠ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ። 

ጀፎረ በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ ብስራትና መርዶን የመሰሉ ማህበራዊ ጉዳዮች የሚካሄዱበትና ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የሚሰጥበት የወል ሀብት ነው።

ስፍራው ማህበራዊ ክዋኔዎች  የሚስተናገድበት የሀገር በቀል ዕውቀትና ጥበብ ማሳያ  ከመሆኑም ባለፈ አሁን ላይ ለቱሪስት መስህብነት በመዋል የኢኮኖሚ ምንጭም እየሆነ ነው። 

ምዕተ-ዓመታት የተሻገረውን ይህን ቅርስ ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ለማዛመድ ከገጠር ኮሪደር ጋር በማስተሳሰር እየተሰራ በመሆኑ ውጤት እየታየበት ነው።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እንዳስታወቀው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀፎረ ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር እንዲተሳሰር መደረጉ የአርሶ አደሩን ማህበራዊ ሕይወትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እያሳለጠው ነው። 


 

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ እንዳሉት ''ጀፎረ'' በጉራጌ ማህበረሰብ ባህልና አሰፋፈር ውስጥ መንደርን  የሚያካፍል  ሰፊ  ጎዳና ነው።

ስፍራው ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የሚከበሩበት፣ የዕርቅ ስርዓት የሚፈፀምበት፣ መተላለፊያና የልጆች መቦረቂያ ሲሆን አረንጓዴና ጽዳቱ የተጠበቀ በመሆኑ የዘመናዊ አኗኗር እሳቤ ማሳያም ነው ብለዋል።

ልማቱ ከጉራጌ ማህበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር የማህበረሰቡን ኑሮ ለመለውጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ካለፈው ዓመት ጀምሮ ጀፎረን ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር ለማስተሳሰር በተደረገው ጥረት በተያዘው ዓመት በዞኑ ከ280 ኪሎ ሜትር በላይ መልማቱን ገልፀው ይህም የአርሶ አደሩን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ አግዟል ብለዋል።

የጀፎረ ልማት የተካሄደባቸው አካባቢዎች ለኑሮ ምቹ ለዓይን ማራኪ አካባቢ በመፍጠር ለቱሪዝም እድገት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑንም ነው ኃላፊዋ ያነሱት።


 

ልማቱ ከተተገበረባቸው አንዱ የሆነው ቸሃ ወረዳ ነዋሪ አቶ በለጠ ወልዴ በበኩላቸው ከገጠር ኮሪደር ልማት ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ ያለው የጀፎረ ልማት አካባቢያቸውን ጽዱ በማድረግ በዘመናዊ መንገድ ለመኖር አስችሎናል ብለዋል።

በጓራቸው እንሰት፣ አትክልትና ፍራፍሬ ከማልማት በተጨማሪ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር ዝርያቸው የተሻሻሉ እንስሳትን ለማርባት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

"የገጠር ኮሪደር ልማት አካባቢውን ገጽታ ውብ ከማድረግ ባለፈ በጓሮ ዶሮ በማርባት እንዲሁም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ አድርጎናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የጌታ ወረዳ አርሶ አደር ፍቃዱ ሰብታጋ ናቸው።


 

የገጠር ኮሪደር ልማት አኗኗቸውን ከማሻሻል ባለፈ የጀፎረ ልማት ታሪካዊ ይዘቱ ሳይለቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እያገዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም