ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫው ያልፍ ይሆን? 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)፦ ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚጫወተው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ ወሳኙንና የመጨረሻውን የዙር መልስ ጨዋታ ዛሬ ከዛምቢያ ጋር ያካሂዳል።

ጨዋታው ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

ሁለቱ ሀገራት ሰኔ 27 ቀን 2018 ዓ.ም በንዶላ ሌቪ ምዋናዋሳ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ዛምቢያ 2 ለ 1 አሸንፋለች።

ፍሪዳ ንዳሼ እና ፒዳ ሙዙዋ የዛምቢያን ጎሎች አስቆጥረዋል። ምኅረት አየለ የኢትዮጵያን ብቸኛ ግብ ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

ጨዋታው በዛምቢያ የተደረገ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ከሜዳቸው ውጪ ያስቆጠሯት ወሳኝ ጎል በአዲስ አበባው የመልስ ጨዋታ የማለፍ ዕድላቸው እንዲለመልም አድርጎታል።

በአሰልጣኝ ራውዳ  አሊ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከመጀመሪያው ጨዋታ መልስ ዝግጅቱን በአዲስ አበባ ሲያደርግ ቆይቷል።

ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያከናወነ ሲሆን ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት እና የስነ ልቦና ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በልምምዱ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ኘሬዝዳንት ዳኛቸው ንግሩ (ዶ/ር)፣ የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባሕሩ ጥላሁን፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሪት ብዙዓየሁ ጀምበሩ እና የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ በመገኘት ቡድኑን አበረታተዋል።

ኢትዮጵያ በድምር ውጤት ካሸነፈች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ ማለፏን ታረጋግጣለች።

በአንጻሩ ዛምቢያ ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ከቻለች ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በዓለም ዋንጫው መሳተፏን ታረጋግጣለች።

በርካታ ደጋፊ በስታዲየሙ በመገኘት ለታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ድጋፍ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሞሮኮ አስተናጋጅነት በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም ለሚካሄደው 10ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዓለም ዋንጫ 24 አገራት ይሳተፋሉ።

የአፍሪካ አህጉር በውድድሩ ላይ በአምስት አገራት የምትወከል ሲሆን፣ ከአስተናጋጇ ሞሮኮ ውጪ አህጉሪቱን ወክለው ወደ ዓለም ዋንጫው የሚጓዙት ቀሪዎቹ አራት አገራት በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ተለይተው ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም