የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 5/2018 (ኢዜአ) ፡-የክልሎች ቅኝት በወፍ በረር
በዚህ ዝግጅታችን በሳምንቱ በክልሎች የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን በወፍ በረር በመቃኘት ማስታወስ ይሆናል። በመሆኑም በዚህ ሳምንት በክልሎች ምን ምን ዋና ዋና ጉዳዮች ነበሩ ስንል እንጠይቃለን?
የኢትዮጵያ እመርታ በምሁራን እይታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ በመሠረተ-ልማትና በማህበራዊ ዘርፎች በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ እመርታ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
የእርሳቸውን ማብራሪያ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ ባለሙያ ከዲር ጀማል (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የብዝሃ ኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫን በመከተል አቅምን አካብቶ በተደመረ አቅም በማልማት ባለፉት አምስት አመታት የተመዘገበው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ሙሐመድ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዝሃ ዘርፍ ላይ ያተኮረ መሆኑ በሁሉም ዘርፎች ተመጣጣኝ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ አግዟል ብለዋል።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊና ስነሰብ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ እንዳልካቸው ጀንበሬ (ዶ/ር)፤ መንግስት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ የነደፋቸው ፖሊሲዎች ሀገር ያላትን ጸጋዎች አልምቶ ለመጠቀም ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማስፋፋትና ለማዘመን ከተያዙ ቁልፍ ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ ዋነኛውና የትኩረት ማዕከል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጥቀሳቸውም ይታወሳል።
ከለውጡ በፊት በሀገሪቱ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ47 በመቶ በታች እንደነበር ጠቅሰው፤ ለዚህም እንደ ፋይናንስ፣ መሬትና የኃይል አቅርቦት ችግሮች በምክንያትነት ይጠቀሱ እንደነበር ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም እያንዳንዱን ኢንዱስትሪ በመጎብኘትና ችግሮቻቸውን በየደረጃው ለመፍታት ባደረገው የተቀናጀ ጥረት፣ ቀድሞ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸው ዛሬ ላይ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር መስፍን መኮንን (ዶ/ር)፤ ባለፉት ዓመታት የውጭ ምንዛሬ እጥረት በትልቅ ተግዳሮትነት የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ችግሩ በፍጥነት እየተቀረፈ ይገኛል ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የግብርናና ምጣኔ ባለሙያ እና ተመራማሪ አደባ ገመቹ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ እንደ ስንዴ እና ሩዝ ያሉ ሰብሎችን በስፋት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ለመቀነስና ለማስቀረት ስኬታማ ስራዎችን ማከናወኗን ገልጸዋል።
የወላይታ ሶዶ እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ዕድል መጠቀም እንደሚገባ የገለጹትን ሃሳብ በመጋራት፤ ለኢዜአ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ምሁራኑ በኮሚሽኑ የተለዩት የምክክር አጀንዳዎች ሁሉንም አካታች አድርገው የተመረጡና ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ተሻለ ተገኔ (ዶ/ር) እንዳሉት በኮሚሽኑ የተለዩ ስምንት የምክክር አጀንዳዎች ለቅራኔ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ የዜጎችን አንድነት በማጠናከር ለሀገራቸው በጋራ እንዲቆሙ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጣሰው ታደሰ ናቸው።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ካሴ በበኩላቸው፤ የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው የመወያያ አጀንዳዎች ስር የሰደዱ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ለሰላም ለተዘረጉ እጆች ምላሽ የሰጡ ወጣቶች ስኬት
የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከጥፋታችን ተምረን ለልማትና ለሰላም ግንባታ አርአያ በመሆን እየሰራን ነው ሲሉ የአማራ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች የገለጹት በዚህ ሳምንት ነው።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተሃዲሶ ስልጠና ወስደው ህብረተሰቡን ተቀላቅለው በልማት ስራ ላይ የተሰማሩ የቀድሞ ታጣቂዎችን የኢዜአ ሪፖርተር አነጋግሯቸዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ፤ በተሳሳተ መንገድ ጫካ በመግባት ማህበረሰባቸውንም ይሁን ቤተሰባቸውን የጎዱበት አጋጣሚ ሲያስታውሱ ከፍተኛ ጸጸት የሚሰማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በጫካ እንዲሰባሰቡ ያደረጓቸው አካላት ለዘረፋና ሃብት ማካበት እንጂ ለአላማ የተሰለፉ እንዳልሆኑ በመረዳታቸውም የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የተሃዲሶ ስልጠና ወስደው ማህበረሰቡን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል። ለሰላም ለተዘረጉ እጆች ምላሽ የሰጡት ወጣቶቹ የልማት አርበኛ እና የሰላም አምባሳደር ሆነው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እየመከረች ነው
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "ሀገራዊ የምክክር ጉባኤውን" ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ማካሄድ ይጀምራል። በምክክር ኮሚሽኑ በተለዩት ስምንት አንኳር አጀንዳዎች ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተመካክረው የሚያቀርቧቸው ምክረ ሀሳቦች በተግባር ተተርጉመው ዘላቂ መፍትሄ ይገኝባቸዋል ተብሎም ታስቧል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአማራ ክልል ሴቶች ማህበራት ፌዴሬሽን ለምክክሩ የተለዩ አጀንዳዎች የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን በመፍታት በአሰባሳቢ ትርክት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚያስችሉ ነጥቦች መሆናቸውን ገልጿል።
የፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር ወይዘሮ እንየ ገነቱ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ታሪካዊ እድል መሆኑን አንስተዋል። የአማራ ክልል ሴቶች ማህበራት ፌዴሬሽን በምክክር ሂደቱ እስካሁንም በንቃት መሳተፉን አውስተው በቀጣይም ለምክክር ጉባኤው መሳካት የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል።
የዲጅታል አገልገሎት ለዘመናዊ የንግድ ስርአት
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ''የተደራጀ የዲጂታል አገልግሎት ለዘመናዊ የንግድ አገልግሎት'' በሚል መርህ የሴክተር ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ አካሄዷል።
በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፤ በበጀት ዓመቱ የንግድ ዘርፉን ከማዘመን በተጨማሪ ዲጂታል አገልግሎቱን በማጠናከር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በተለይም የተገልጋዩን ጊዜና ጉልበት ለሚቆጥቡ አገልግሎቶች ተደራሽነት የተደረጉ ጥረቶች ስኬታማ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ የንግድ ፈቃድና መሠል አገልግሎቶችን በኦን ላይን በመፈጸም የንግዱን ማህበረሰብ የአገልግሎት እርካታ 96 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ 805 ተጨማሪ የቅዳሜ እና ዕሁድ ገበያዎች መከፈታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን ለማህበረሰቡ በቀጥታ ማቅረብ በመቻሉ ገበያው እየተረጋጋ መምጣቱን አንስተዋል።
በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ማንሳታቸው ይታወሳል።
ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት
ሳምንቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በስፋት የተተገበረበትም ነው።
የዘንድሮው ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት "በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በሀዋሳ ከተማ የተካሄደው በዚህ ሳምንት ነው።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴቶችን በማጎልበት ማህበራዊ ሃላፊነት በጋራ መወጣት የሚያስችል ነው።
በመርሃ ግብሩ ወጣቶች የሚያከናውኗቸው የልማት ተግባራት ህዝቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ህብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ በበኩላቸው በጎነትና አብሮነት የማህበረሰቡ መልካም እሴት በመሆኑ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶች እርስ በርስ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ባከናወኗቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው።
በዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 25 ሚሊዮን ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች በመሳተፍ ከ53 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ተግባራትን እንደሚያከናውኑም ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትም የክልሉ እና የዞኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻ እንደገለፁት፤ የህዝቡን የነበረውን የቆየውን የመረዳዳት እሴትና ባህል ወደነበረበት ለመመለስ የክልሉ መንግስት እየሰራ ይገኛል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በበጎ ፍቃድ አገለግሎት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶቾ፣ የአረጋውያን እንክብካቤን ጨምሮ በአቅመ ደካማ ቤት እድሳትና ግንባታ፣ በደም ልገሳ፣ በፅዳት፣ በውበትና በአረንጓዴ አሻራ ህዝቡ የነበረው ተሳትፎ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን አመላክተዋል።
ተስፋን እንትከል
ሳምንቱ የክረምቱ ዝናብ ያየለበትና የእርሻውና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላው መርሃግብር በስፋት የተካሄደበት ሆኖ አልፏል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በፓርላማ ጊቢ ከተከሉት ችግኝ ጀምሮ በመላ ሀገሪቷ በስፋት የተተከለበት ሳምንት ነው።
በሳምንቱ የክልል አመራሮች፣ የተቋማት ተወካዮች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ነዋሪዎች ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በስፋት ተክለዋል።
8 ቢሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የሚተከሉበት የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቢሾፍቱ ሆረ አርሰዴ ሀይቅ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ ማስጀመራቸው ይታወሳል።
ቦሎቄን በኩታ ገጠም
በኦሮሚያ ክልል የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ የሚረዱ እና ለወጪ ንግድ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት የማምረት ስራ ትኩረት ማግኘቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገለጹ።
በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ ቦሎቄን በኩታ ገጠም የመዝራት ሥራ የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተገኙበት ተጀምሯል።
በዚሁ ወቅት የቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አዱኛ በክልሉ የግብርና ምርታማነትን በእጥፍ ከመጨመር ጎን ለጎን፣ የአርሶ አደሮችን ገቢ ለማሳደግ በወጪ ንግድ ምርቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ ቦሰት ወረዳ የዶንጎሬ ጪዮስ ቀበሌ የተጀመረው ቦሎቄን በኩታ ገጠም የመዝራት ሥራ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው መሰል መልካም ተሞክሮዎች እንዲሰፉ ይደረጋል ነው ያሉት።
በደቡብ ወሎ ዞኑ 15 የእርሻ ትራክተሮች ለአርሶ አደሩ የተከፋፈሉትም በዚሁ ሳምንት ነው።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮነን በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፤ በዞኑ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዘግቦበታል።
ዞኑ በሜካናይዜሽን ለሚካሄድ የሰብል ልማት ምቹ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ጥራትና ብዛት ያለው ምርት በማምረት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ስርጭት
በአማራ ክልል ለመጪው መኸር ሰብል ልማት የሚውል ከአራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለዘንድሮው የመኸር ሰብል ልማት 8 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
እስካሁን ባለው ሒደትም ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ወደ አካባቢው የገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነውን ለአርሶ አደሩ ማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
የማዳበሪያ ስርጭቱ ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎችንና በክረምት ለተሽከርካሪ አስቸጋሪ ለሆኑ አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን
በጎንደር ከተማ ገጠር ቀበሌዎች የተጀመረው ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር ግንባታ በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በ2019 በጀት ዓመት አሻጋሪ የእድገትና የዘላቂ የልማት እቅድ ዙሪያ ከአጋር አካላት ጋር የትውውቅ መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ፕላንና ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ፋሲል አብዩ እንደተናገሩት የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ከመቀየር ባለፈ ሁለንተናዊ አገልግሎትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
የገጠር ኮሪደር ልማት መሰረተ ልማትን በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ እና የግብርናውን ኢኮኖሚ ለማዘመንም ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።
በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሳይ እና በሳቢያ የገጠር ቀበሌዎች በገጠር ኮሪደር የተገነባውን ሞዴል የአርሶ አደሮች መንደር በአዲሱ በጀት ዓመትም በሌሎች ቀበሌዎች ለማስፋት የቅድመ ዝግጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአስተዳደሩ ስር በሚገኙ 11 የገጠር ቀበሌዎች 20 ሞዴል የገጠር መንድሮችን ለመገንባት ዝግጅት መጀመሩንም አቶ ፋሲል ጠቅስዋል።
የማዕድን ሀብት ልማት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ ሀገሪቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከወርቅ ማዕድን ዘርፍ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ ገቢ ማስመዝገቧን ይፋ አድርገዋል።
በማዕድን ዘርፍ የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ እና ድጋፍ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻሉንም አስታውሰዋል።
የማዕድን ሀብት ክምችት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የማዕድን ምርት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናስር ሙሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ወርቅን ጨምሮ በርካታ ማዕድናትን በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ ከመቻሉ በላይ ክልሉ ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።
ለአብነትም በ2018 በጀት ዓመት 8 ሺሕ 961 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መግባቱን ገልጸዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም በበጀት ዓመቱ 348 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ አስታውቋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ወልያብ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 350 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለማቅረብ ታቅዶ 348 ኪሎ ግራም ምርት ቀርቧል።
በጥራትና በፍጥነት የፕሮጀክቶች ግንባታ
በሶማሌ ክልል የተጠናቀቀውን የ2018 በጀት ዓመት የሴክተር ቢሮዎች የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በጅግጅጋ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ እየተገነቡ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራት ተጠናቀው ለአገልገሎት እንዲበቁ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የክልሉ እና የሀገሪቱን ልማት ማፋጠን የሚችል ብቁ የሰው ሀይል እንዲያፈሩ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችም ይጠናከራሉ ሲሉ ተናግረዋል።
መሰረተ ልማት
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 40 ሺህ አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያስታወቀው በዚሁ ሳምንት ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ ይህን የተናገሩት የሞጆ-አዳማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ወቅት ነው።
ፕሮጀክቱ ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን አዳማ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ማዕከል እንደመሆኗ፣ ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አስር ዓመታት የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 40 ሺህ አዳዲስ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ከ25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ከእነዚሁ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ የጎዴና ቢቸና ከተሞች የውሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።
ማጠቃለያ
ሳምንቱ በሁሉም ክልሎቻችን መደበኛ የልማት፣ የማህብራዊ እና የሰላም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው የቀጠሉበትም ነበር። በሁሉም ክልሎች የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተሳካ ሁኔታ በመካሄድ ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ ተከላና የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት በሁሉም ክልሎች እየተከናወነ ይገኛል።