ቀጥታ፡

የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)፡- የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የአሶሳ ከተማ የመጀመሪያው የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ "ለኮሪደር ልማትና ለከተማ ውበት እሮጣለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ ማለዳ ተካሂዷል።


 

በመርሃግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገፅታ በመቀየር የተለያዩ አገልግሎቶች ለነዋሪዎች ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል።

የአሶሳ ከተማ የኮሪደር ልማትም ከተማዋን በማዘመን ለነዋሪዎቿ ምቹ እንድትሆን ከማድረግ ባለፈ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ በታዎችን በመገንባት ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

በዚህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተለዬ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፥ የዛሬው የጎዳና ላይ ሩጫም የኮሪደር ልማቱ ለስፖርቱ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ይበልጥ የሚያመላክት ነው ብለዋል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም መንሱር በበኩላቸው፤ መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በርካታ የስፖርት መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑን አንስተዋል።

እንደዚህ ዓይነት የጎዳና ላይ ሩጫ የአትሌቲክስ ስፖርትን ከማነቃቃት ባለፈ በህዝቦች መካከል ያለውን ማህበራዊ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።


 

በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ሯጮችም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም