ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ከተማ የወል ትርክት ግንባታን በማጎልበት የሰላምና የልማት ማዕከል እየሆነች ነው

አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባ ከተማ አሰባሳቢና የወል ትርክት ግንባታን በማጎልበት የሰላምና የልማት ማዕከል እየሆነች መምጣቷን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በዓድዋ ድል መታሰቢያ የምክር ቤቱ መሰብሰቢያ አዳራሽ እያካሄደ ይገኛል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ የከተማ አስተዳደሩን የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት እያቀረቡ ነው።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሪፖርታቸው፤ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብ እናደርጋታለን ብለን በገባነው ቃል መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ መሠረታዊና ሥር ነቀል ለውጦችን ማከናወናን ችለናል።

በተጨማሪም ሥር የሰደዱ ኋላቀር አስተሳሰቦችንና ችግሮችን በጽናት በመጋፈጥ፣ አዲስ አበባን ከማይጠቅም የመሳሳብና የመገፋፋት ፖለቲካ የተላቀቀች የሰላምና የልማት ማዕከል ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ለአብነትም የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመገንባት አሰባሳቢና የወል ትርክት ለማስረጽ የሚያስችሉ መሠረቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ ውብ፣ አረንጓዴና ጽዱ በመሆን ለኢትዮጵያ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን የሚያስችሉ መሠረቶችን እየጣለች እንደምትገኝ አስረድተዋል።

የመዲናዋን ጎስቋላ ገጽታ በመቀየር ከተማዋ ከአፍሪካ አስር ጽዱ ከተሞች አንዷ በመሆን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቷን አንስተዋል።


 

የመዲናዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱም ሌላው የመሠረታዊ ለውጥ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ መንገዶቿ ሰፊ፣ የነበረችበት የጨለማ ገጽታም ወደ ብርሃን መቀየሩን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ይህም ከተማዋ በርካታ ኮንፈረንሶችንና ጎብኝዎችን የማስተናገድ ብቃቷን እንዳሳደገው አብራርተዋል።

የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷም ይበልጥ ጎልብቶ፣ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያን ዋና ከተማችን ብለው የሚጠሯትና የሁላችንም ኩራት መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም