ቀጥታ፡

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው

ሚዛን አማን፣ ሐምሌ 5/2018 (ኢዜአ)-:-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተገልጋዮች ገለጹ፡፡

በክልሉ በሁለተኛ ዙር የተገነቡ አምስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በቅርቡ ወደሥራ የገቡ ሲሆን በሦስተኛ ዙርም 15 አዳዲስ ማዕከላት ለመገንባት መታቀዱ ተመላክቷል።


 

በክልሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሚዛን አማን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዮች እንደገለጹት በማዕከሉ ቀልጣፋ፣ ከብልሹ አሰራር የጸዳና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡

ከተገልጋዮች መካከል አቶ ከረጋ ወልደማርያም  በማዕከሉ የባንክ እና ዲጂታል መታወቂያን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መስተንግዶ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።


 

የጤና ሙያ ፍቃድ ለማሳደስ ወደማዕከሉ እንደመጡ የገለጹት ወይዘሮ ቤዛዊት ጠና በበኩላቸው በማዕከሉ ባገኙት ቀልጣፋ መስተንግዶ በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ማዕከሉ ከመከፈቱ በፊት የጤና ሙያ ፍቃዳቸውን ለማደስ ረጅም ኪሎ ሜትር ይጓዙ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው ማግኘት መቻላቸው ትልቅ ለውጥ እንደሆነና ገንዘብና ወጪንም እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

መንግስት ለሕዝብ የቀረበና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰራርን ከማዘመን ባለፈ የጊዜና ጉልበት ብክነት ማስቀረቱን የገለጹት ደግሞ አቶ ስማቸው መኮንን እና ወጣት ሀፊዝ ሁሴን ናቸው። 


 

ዲጂታል መታወቂያ ለማውጣት በማዕከሉ መገኘታቸውን ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም ሲገጥማቸው የነበረ የቀጠሮ ምልልስና ሌሎች ችግሮች ተፈተው ፈጣንና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ አህመዲን አወል በበኩላቸው መንግሥት የሕዝብ አገልግሎትን ከእንግልትና አድሏዊ አሠራር ነጻ ለማድረግ የዘረጋው ዘመናዊ አሠራር ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።


 

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ35 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰው የተገልጋይ ቁጥርና እርካታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በክልሉ የዲጂታል አሠራሩን በማስፋፋት ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በማለም በሁለተኛ ዙር 5 ተጨማሪ ማዕከላት ተገንብተው ሥራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በማዕከላቱ እየተገኘ ያለውን ውጤት ለማስቀጠል የህዝብን ተጠቃሚነት ለማስቀጠል በሦስተኛ ዙር 15 አዳዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት በተለያዩ የክልሉ ከተሞች በቅርቡ እንደሚገነቡም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም