ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የልዩነቶቻችን ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በምክክር ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት ይሆናል-ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ - ኢዜአ አማርኛ
ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የልዩነቶቻችን ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በምክክር ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት ይሆናል-ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ የልዩነቶች ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በሰለጠነ ምክክር ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበት እንደሚሆን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።
ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ይህን የገለጹት ኮሚሽኑ ያዘጋጀውና "ኢትዮጵያ እየመከረች ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ በሚገኘው የ5 ኪሎ ሜትር ታላቁ የሩጫ ውድድር ላይ ነው።
በዚሁ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት፤ ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት በሙሉ ተጠናቋል።
ለዚህም በዋናው ምክክር ላይ የሚሳተፉ ተመካካሪዎች ከሁሉም ወረዳዎች፣ ክልሎች እንዲሁም ከሀገር ውጭ ጭምር አዲስ አበባ መግባታቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
በዋናው የምክክር ጉባኤ በዜጎች መካከል የልዩነት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ወኪል ተመካካሪዎች መክረውና ዘክረው ዘላቂ መፍትሔ በሚሰጡ ሐሳቦች ላይ መግባባት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
ምክክሩ ለዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ እንዲበቃ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የጸጥታ ተቋማት፣ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግሥት አካላት፣ ለሲቪል ማኅበራትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ የሚካሄድ ሲሆን፤ በጉባኤው ላይ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ይመከርባቸዋል።
የዋናው ጉባኤ የምክክር ዐበይት አጀንዳዎች የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች (አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ጉዳይ፣ የሃይማኖት ጉዳዮች፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች (የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳይን ጨምሮ)፣ ሙስና፣ መልካም አስተዳደርና የሰላም ግንባታ የሚሉት ናቸው።